ሴቲቱ ማን ናት?

ሴቲቱ ማን ናት?

“ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች” (ራእይ 12፡1)

ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ

ታላቅ ምልክት የተባለችው ድንግል ማርያም ናት፡፤ በሰማይ መታየቷ ሰማይ፣ ከሁሉም በላይ ሆኖ ከፍ ብሎ እንዲታይ እመቤታችንም ልዕልት መሆኗን ያመለክታል፤ ከሴቶች ሁሉ የተለየች የመሆንዋ ምሥጢርም ይህ ነው (ሉቃ 1፡28)፡፡ ምልክቲቱ የተሰጠችው በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ሲያሳይ ይህም በትንቢት “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትጸንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለለች (ኢሳ 7፡14) የተባለው ለመፈጸሙ ማሳየቱን ነው፡፡

ፀሐይ የተባለው እግዚአብሔር ነው (መዝ 26፡1፣ ዮሐ 8፡12)፡፡ ፀሐይ የብርሃን ምንጭ እንደሆነ ከእርስዋ የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የፍጥረት ሁሉና የመዳን ምንጭ እርሱ ብቻ ነው፤ እርስዋ ተጎናጽፋው ማለት ጌጧ ሆኖ፣ ልጇ ሆኖ “ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” (ሉቃ 1፡28) እየተባለች፤ አብርታ ደምቃ ታየች፤ በመወለዱም በጨለማ የምንሄድ ሕዝብ ብርሃናችንን እርሱን አየን (ማቴ 4፡14-16፣ ሉቃ 1፡78፣ ዮሐ 1፡8፣ ዮሐ 9፡5፣ ራእይ 21፡23)፤ እርሱ ብርሃን ተብሎ እናቱን እመ ብርሃን (የብርሃን እናት)፣ አሰኝቷታል፡፡ መጎናጸፍዋ በብርሃን የተሞላች መሆንዋን ያመለክታል፤ ይህም “በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻል” (ሉቃ 1፡30) “ጸጋን የተሞላሽ” የተባለች ሌላ ከሰው ወገን ስለሌለ ፀሐይን ተጎናጽፋ ተባለች ይህም ክብርዋ ነው፡፡

ጨረቃን ከእግሮችዋ በታች ያላት

ፀሐይ የአዳኛችን የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል፡፡ ጨረቃ በተፈጥሮ የራሱ ብርሃን የለውም፡፡ የዚህ ምሳሌ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፡፡ ዮሐንስ ወንጌላዊ አስቀድሞ በወንጌሉ የጻፈውን ስንመለከት “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ፤ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም” (ዮሐ 1፡6-9) በማለት ከብርሃን የሚያንሰው ዮሐንስ መጥምቁ እንደሆነ የተናገረውን በድጋሚ በራእዩ አየው፡፡ ፀሐይ የራሱ ብርሃን እንዳለው፤ ጌታ የባህርይ ብርሃን ነው፡፡ ጨረቃ የራሱ ብርሃን እንደሌለው፣ ብርሃንን ከፀሐይ እንደሚቀበል፤ መጥምቁ ዮሐንስ የጸጋ (የስጦታ) ብርሃንን ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጸጋ ይወስዳል፡፡ ጨረቃ ብርሃኑ እያነሰ እያነሰ እንደሚመጣ፤ የዮሐንስም የስብከት ጊዜ እያበቃ እየተፈጸመ፣ የጌታ ትምህርትና ብርሃን እየታወቀ እየጎላ እንደሄደ ራሱ ዮሐንስ መጥምቁ ተናግሯል፡፡ “ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል” (ዮሐ 1፡15) በሌላም ቦታ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” (ዮሐ 3፡30) በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ሴቲቱ ጨረቃን ከእግርዋ በታች አድርጓ መታየቷ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ከሌሎቹ ነቢያት ምንም ቢበልጥ ከእርስዋ ግን ያነሰ ለመሆኑ፤ በጽንሱ ጊዜ ድምጽዋን ሲሰማ ለምትበልጠው ለጌታ እናት በደስታ መዝለሉን ያሳውቀናል (ሉቃ 1፡44)፡፡

በራስዋም ላይ የ12 ከዋክብት አክሊል የሆነላት

እነዚህ 12ቱ ሐዋርያት ናቸው፡፤ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ስትሆን፤ እነርሱ በከዋክብት ይመሰላሉ፤ ብርሃኑን የሰጣቸው ልጇ ነው፡፡ እርስዋ ፀሐይን ስትጎናጸፍ እነርሱ በብርሃን ክርስቶስ አምነው ያጌጡ ምስክሮቹ ናቸው፡፤ እርሱን ተወለደ ቤዛ ሆነ ብለው ሲመሰክሩ የእርስዋን ስም እያነሱ ከድንግል ሴት ተወለደ ብለው የመመስከራቸው ምሳሌ ነው (ገላ 4፡4)፡፡ እርስዋን ይዘው ወደ ጌታ ይጸልያሉ “እነዚህ ሁሉ ከኢየሱስ እናት ከማርያም … ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር” (ሐዋ 1፡13-14) በዮሐንስ ወንጌላዊ አማካኝነት ከመስቀል ስር ያገኙአት የአደራ እናታቸው ናትና (ዮሐ 19፡26-27)፡፡

እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች (ራእይ 12፡2)

የሔዋን ባህርይ ያላት ናት እንጂ፣ ኃይለ አርያማዊ (የሰማይ መላእክት ወገን) አይደለችም፣ ለማለት ሲያስቀምጥ፣ በሌሎች ሴቶች ልማድ ጭንቅ እንደአለባቸው ተናገረ እንጂ በእርስዋስ ጭንቅ የለባትም፤ ጭንቅ የሚሆንባት ቀጥሎ ያለው የበረሃ ስደት በነፍስዋ እንደሚያልፍ ዮሐንስ የተገለጸለትን መናገሩ ነው፡፡

ያለ ጭንቅ እንደተወለደ የምናምንበት ምክንያት፤ ዋናው እግዚአብሔር የድንግል ማርያምን መብት ለመንካት ከሰማይ አልወረደም፤ ድንግል በድንልና መኖር ስትመኘው የነበረው ነው፡፡ ስለዚህም ነው “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” (ሉቃ 1፡34) እያለች የድንግልና ፍላጎትዋን የምትናገረው፤ እርስዋ በድንግልና ኖሯ በድንግልና ነው የወለደችው፡፡ እዚህ ላይ ከመጽነስዋ በፊት ሁሉም ድንግል መሆንዋን ያምናል፤ ነገር ግን ድንቅ ሠሪውን እግዚአብሔርን በመጠራጠር፣ እንዴት ሥጋ ሆኖ ሲወለድ ድንግልናዋ አልጠፋም? ብለው የሚጠይቁ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ልብ ወለድ ጥያቄአቸውን በጥያቄ እንመልስላቸዋለን፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ድንጋይ ሳይፈነቅል ከሙታን ተነሥቶ ወጥቶአል፡፡ መልአኩ ነው መጥቶ “ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ” “እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም” ብሎ መነሣቱን ያሳያቸው፡፡ እንዴት ድንጋዩን ሳይገለብጥ ጌታ ወጣ? በተጨማሪም ሐዋርያት በራፋቸውን ዘግተው ሳለ እንዴት ሳይከፍት ገባ? (ማቴ 28፡1-5፤ ዮሐ 20፡19)

መልሱ “የሚሳነው ነገር የለም” ከሆነ ከድንግል ማርያምም በድንግልና ለመጸነሥና ለመወለድ የሚሳነው ነገር ስለሌለ ተዘግቶ የሚኖር የእግዚአብሔር የ9ወር ከ5 ቀን መቅደስ ማሕጸንዋ ተዘግቶ እንደሚኖር የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም በድንግልና ነው የተወለደው ስለዚህ እርስዋ ያለ ጭንቅ ነው የወለደችው (ሕዝ 44፡1-2)፡፡

የመጽሐፍት አካሄድ በሌሎች ልማድ ያለውን ለሌላ ሰጥተው ይጻፋል፡፡ የድንግል ማርያምም የብዙ ሴቶችን ልማድ ለእርስዋ ሰጥቶ መናገሩ ሴት መሆንዋን ለመግለጽ እንጂ ጭንቅስ የለባትም፡፡ ለምሳሌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰዎችን አጥምቆ ያውቃል? አያውቅም? “ወደ ዮሐንስም መጥተው። መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት” (ዮሐ 3፡26) ይላል፡፡ ያው ዮሐንስ በጻፈው ወንጌል መልሶ ያጠምቃል ያሉት የሌሎችን ሥራ ለእርሱ ሰጥቶ መናገር መሆኑን “ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም” (ዮሐ 4፡2-3) ይላል፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ አካሄድ ብዙ ሴቶች በጭንቅ ይወልዳሉና፤ የሴቶችን ለድንግል ማርያም ሰጥቶ የናገር ልምድ ነው፡፡

ድንግልም ያው ሴት ናት ሔዋናዊ ሥጋን የለበሰች፤ የሰው ወገን ነች ለማለት “እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች” አለ፡፡ በድንግል ማርያም የእርግማን ውጤት የለባትም በምድር ላይ እንደ እርስዋ የሆነ ሴት የለም፤ ተወዳዳሪ የሌላት ብርክት እንጂ ርግምት እንዳልሆነች “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” (ሉቃ 1፡28) ተብላለች፤ ይህን ያላት ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ ከእግዚአብሔር የተላከ የእግዚአብሔርን ቃል ነው የሚናገረው፤ ያው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በኤልሳቤጥ አድሮ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” (ሉቃስ 1፡42) የተባለችውን እናት እርግማን አለባት ለማለት ቁጭ ብድር ሲሉ ትንሽ ስቅጥጥ አይላቸውም? በትንቢት “ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም” (መኃልይ 4፡7) የተባለችን እናት፤ እርግማን እንደሌለባት ያሳየናል፤ በዚህ “ምጥ” በሚለው የሴቶች ልማድ ሴት ናት ለማለት የተጠቀሰ ነው፡፡

ዘንዶው በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን ሊበላ በፊትዋ ቆመ (ራእይ 12፡4)

ዘንዶው እያለ የሚናገረው፣ በቀጥታ ዘንዶ አይደለም፤ ይህ በእግዚአብሔር መጽሐፍ አገላለጽ የተለመደ ነው፡፡ “እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” (ማቴ 23:33) በሚለው ውስጥ እናንተ እባቦች ያላቸው በተንኮል የሚታወቁትን ሰዎችን እንጂ የተፈጥሮ እባቦችን አይደለም፡፡ እንዲሁም በዚህ ቦታ ታላቅ ዘንዶ የተባለው ጌታ ሲወለድ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ነው፡፡ “ጌታ ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ . . .ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ … ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ። ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው” (ማቴ 2፡1-8) ይህ አነጋገር ሊሰግድለት ሳይሆን በቅኔያዊ አነጋገር በእባባዊ ተንኮሉ ሕፃኑን ለመግደል ስለፈለገ በራእይ “ሕፃንዋን ሊበላ” በሚል ቃል ለቅዱስ ዮሐንስ ተገልጾለታል፡፡

በፊትዋ መቆሙ የድንግል ማርያምን አንድ ልጅዋን ሊገድለው መወሰኑን ያሳያል፡፡ ይህም የንጉሠ ነገሥቱ የክርስቶስ መወለድ ያስቆጣው እንደሆነና በዚህም ውጤት “ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ” ይህ እርምጃ ከሚገደሉት ሕፃናት መካከል አንዱ ጌታ ኢየሱስ ይሆናል የሚል ግምትን ያሳያል (ማቴ 2፡10)

አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ
ወንድ ልጅ ወለደች (ራእይ 12፡5)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም በተወደደ በጽኑዕ ሥልጣኑ መጠበቁን የሚያመለክት ሲሆን ይህም አስቀድሞ ከጽዮን ድንግል ማርያም ላይ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋ ነፍስ ላይ ተሹሞ እንደሚገዛ የተተነበየውን ያስታውሰናል፤ “እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ…ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ” (መዝ 2፡9) እንዲል፡፡ በተመሳሳይም ለዮሐንስ በራእዩ ሲገልጽለት፤ “ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፡፡ በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል፡፡ ….በብረት በትር ይገዛቸዋል፤…በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት። የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው” (ራእይ 19፡12-16) የተባለውን መሆኑን ስለሚገልጽ ይህን ባለ ግርማ ንጉሥ የወለደች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሌላ ሴት የለችም፡፡

ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ (ራእይ 12፡5)

መጽሐፍ ቅዱስ የድንግል ማርያም ልጅ በሰማይ እንደሚኖር በግልጽ ከተናገረ፤ ይህ “ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ” የሚለውን ለሌላ ሴት ልጅ፣ ልንሰጠው በፍጹም አይገባም፤ ምክንያቱም “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው (ዮሐ 3:13) ብሏልና፡፡ የሰው ልጅ የሚለው ደግሞ ከሰው ወገን እርሱን የወለደች ሌላ ከሌለች መጽሐፍ “ከኢየሱስ እናት ከማርያም” (ሐዋ 1፡14) ካለን፤ እናት የሆነችው ሌላ ባለመኖርዋ ሴቲቱ ድንግል ማርያም መሆንዋ ግልጽ ነው፡፡

ወደ ዙፋኑ፣ በሚለው አገላለጽ ውስጥ ባለ ዙፉን፣ የነገሥታት ንጉሥ መሆኑን ያሳውቀናል፡፡ ስለዚህ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ግርማው ነው ሄዶ የተቀመጠው፡ “ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” ይላልና (ዕብራ 1፡3)፡፡ “ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ” (ሐዋ 1:11) አስቀድሞ በትንቢት፣ ራሱ እግዚአብሔር ሊያድነን ተወልዶ፣ ያንኑ የተዋሐደውን ሥጋ ይዞ ወደ ሰማይ እንደሚያርግ በልበ አምላክ በዳዊት አንደበት “በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” (መዝ 67:33)፣ “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ” (መዝ 46:5) በመባል ተተንብዮአል፡፡ ይህን ትንቢት ሊፈጽም ጌታ “ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ” (ሉቃስ 24:51) “በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ” (ማር 16:19)፡፡ ልብ እናድርግ ልጅዋ እንዲህ ወደ ሰማይ ከወጣ፡፡ የዚህ ባለ ሥልጣን እናት ድንግል ማርያም ብቻ ናት፡፡

ሴቲቱም ወደ በረሀ ሸሸች (ራእይ 12፡6)

“ሴቲቱም ወደ በረሀ ሸሸች” ሲል ከእርስዋ ጋር ልጅዋ ዮሴፍና ቅዱሳን መላእክት መኖራቸው አይካድም፡፡ ምክንያቱም ሊናገሩለት በፈለጉት አስጠጋግቶ መናገር የመጽሐፍ ልማድ ነው፡፡ ለምሳሌ “ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም አበዛሁትም” (ኢሳ 51:2) በሚለው ውስጥ ብቻውን የሚለው ቃል ብቻ አንድን አያመለክትም፤ ሚስቱን ይዞ ነው የተጠራውና፤ ከእርሱም ጋር የወንድሙ ልጅ ሎጥ ነበረ፡፡ በዋናው መናገር ልማድ ነው፡፡

ሌላም ምሳሌ ብናይ “አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ” (ሕዝ 33:24) ከእርሱ ጋር ሚስቱ አሸከሮች ከእርሱ ጋር የተሰደዱ ዘመዶቹ አሉ፡፡ በአዲስ ኪዳንም “አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ።” (Ebera 11:8) የሚለው በአንድ ሰው አንቀጽ ነው በዋናው ሌሎችን አጠቃልሎ መናገር የመጽሐፍ ልማድ መሆኑን ልንረዳ ይገባል፡፡

የስደተኞች እናት ስደትን ልትባርክ፣ ከልጅዋ ጋር በረሀ ለበረሃ ተንከራታለች፡፡ ለዚህ ነው “ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ” በሚለው ውስጥ ዝግጅቱ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረ ስለመሆኑ፡- “ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት” (ሆሴዕ 11፡1) ይላል፡፡ በዚህ መሠረት ስለመሰደዱ ወንጌላዊው ማቴዎስ ሲጽፍ፣ “የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ” (ማቴ 2፡13-15)፡፡ ልጇን ከእባቡ ሄሮድስ ለማዳን የግብፁን አሸዋ ግለት፣ የውኃውን ጥም፣ ርሃቡን ሁሉ ታገሰች፡፡ በራእይ ላይ እንዲህ የተባለች ሴት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሌላ ሴት የለችም፡፡ “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ማቴ 5፡10) ይህን “ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን…ወደ በረሀ ሸሸች” የሚለውን የሚፈታልን ራሱ እዚያው ዮሐንስ ነው፡፡ ይህ “አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ” መሄድዋን ያመለክታል፡፡ ይህም ድንግል ማርያም ይህን ያህል ዘመን በበረሃ ቆይተው እንደመጡ የሚናገረው የታሪክ መጽሐፍዋ ጋር አንድ ነው፡፡

ዘንዶውም… ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት (ራእይ 12፡13)

በነቢዩ በኢሳይያስ አስቀድሞ “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና” (ኢሳ 9፡6) የተባለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ኃያሉን ልጅ በመውለዷ፣ እርሱን መቋቋም ቢያቅተው፤ ከእርስዋ ሥጋ ነሥቶ ነው ድል ያደደረገኝ በማለት ምክንያተ ድኂን፣ መሠረተ ሕይወት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ዘንዶው ማሳደድ ጀመረ፡፡ ለጊዜው በሄሮድስ አድሮ ኃያል ወልድን የወለደች እመቤታችንን ወደ ግብጽ ያሳደዳት ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከሰው ልጆች ልቦና ውስጥ የእመቤታችንን ፍቅሯን፣ አማላጅነትዋንና የጸጋ እናትነትዋን ለማስወጣት እያሳደደ ይገኛል፡፡

በዚህ ዘመን ልብ ይስጣቸውና እንደ ሄሮድስ ሰይጣን ያደረባቸው ሰዎች፤ ልጇን እፈልጋለሁ፣ እርስዋን ግን አንፈልግም የሚሉን ሁሉ እናቱን መቀበል ማለት ልጇን መቀበል መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፤ (በማቴዎስ 10፡40-42) “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል” ያላቸውን ሐዋርያትን እንኳ የተቀበለ፣ ላኪውን ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበለ ከሆነ፤ እናቱንማ መቀበል እንዴት ልጅዋን መቀበል አይሆን?

“ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል” ካለን፣ ድንግል ማርያምም ይህ ማዕረግ አላት፤ እርስዋን መቀበል፣ የእርስዋን የስደትዋን ዋጋ፣ የጸሎትዋን ዋጋ እንቀበላለን ስንላቸው፣ እንዴት አታገኙም ሊሉን ይችላሉ? “ቀዝቃዛ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙሬ ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም” እያለን፣ እርስዋ ከደቀ መዝሙርነትም አልፋ እናቱ ናት፣ በእርስዋ ስም ብናበላ ብናጠጣ ዋጋ አታገኙም ለምን ይሉናል? ይህ ሁሉ ከንቱ ድካም፣ በስጦታ (በጸጋ) እናታችን የሆነችውን የአምላክነን እናት (ዮሐ 19፡26) ከልባችን ሊያሳድዱ መፈለጋቸውን ያሳያል፡፡

ስለ እርስዋ አማላጅነት ሲነሣ ቁጭ ብድግ እያሉ የሚቃወሙ እኒህ የዲያብሎስ ጀሌዎች፤ ይህን ጠላትነት ከዘንዶው ካልሆነ በቀር ከየት ሊያገኙት ይችላሉ? በቃና ዘገሊላ ማማለዷን ሲቃወሙ የነበሩ ሰዎች፤ አሁን አሁን በሥጋ ሳለች ይሁን እንቀበለው አማልዳለች፤ አሁን ግን የለችም፣ አታማልድም ይሉናል፡፡ ልብ ልንል የሚገባው ሐዋርያትን “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡” (ማቴ 28፡20) ያለው ጌታ አሁን እነርሱ በሥጋ ኖረው አይደለም፤ በነፍስ ስላልሞቱ አሁንም ከእርሱ ጋር ስላለ ነው፡፡ ከእመቤታችንም ጋር አብሮ ለመኖሩ በመልአክ አንደበት “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” (ሉቃ 1፡28) ካላት ከእርስዋ ጋር እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለመኖሩ ምን ጥያቄ አለው፡፡ እርስዋ በነቢዩ እንደ ተነገረው “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ተብላለችና (መዝ 44፡9) ማንም ከልባችን ሊያሳድዳት አይችልም::

እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት (ራእይ 12፡14)

የታላቁ ንሥር የተባለው አባቷ አብርሃም ነው፡፡ አብርሃም በሁለት ክንፎቹ የተመሰሉት ምግባርና ሃይማኖቱ ናቸው “እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ” (ያዕቆብ 2:21-23)፡፡ ክንፍ በቀጥታ ክንፍ ተብሎ እንደማይተረጎም ለመረዳት፣ ለምሳሌ ”በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል” (ዘጸ 19:4) “በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ” (መዝ 16፡8) “በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ” (መዝ 17፡10) “ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም” (ማቴ 23፡37) በሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች ውስጥ እግዚአብሔር ክንፍ አለው ብለን እንደማንተረጉም የታወቀ ነው፣ ምሳሌ እንጂ፡፡

ስለ ሰዎች በተነገረውም “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ” (ኢሳ 40:31) ሲባል ክንፍ አውጥተን እንበራለን ማለት እንዳልሆነ፣ እንዲሁ ድንግል ማርያም የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት ሲባል ክንፍ አላት ማለት አይደለም፣ ምግባርና ሃይማኖትዋን በክንፍ መሰሎት ነው፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም ሃይማኖትዋ ጽኑ በመሆኑ፤ ከቤተ መቅደስ ስታድግ ስለ አምላክ መወለድ በእምነት ስትጠባበቅ የኖረች ከመሆንም አልፎ ያቺ ድንግል ሴት ላይ ደርሼ እያገለገልሁ ከእርስዋ ጋር በኖርኩ ማለትዋ የምግባርዋን ትሕትና ያሳያል፡፡ ለዚህም ነው ይህን ትሕትናዋን መጽሐፍ ጽፎ ሲያስቀምጥልን “የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአል” በማለት የገለጠችው (ሉቃ 1፡48)፤ ስለ አማኝነትዋ አክስትዋ ኤልሣቤጥ “ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት” አለቻት (ሉቃ 1፡45)፡፡

እኛም ልጆችዋ እኒህን ሁለት አክናፎች ሊኖረን ይገባናል፡፡ ሃይማኖት አለኝ በማለት ብቻ አይዳንምና፡፡ ምግባር የሌለው ሰው እምነቱ ምን ይጠቅመዋል? “አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም:- አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ።…ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው። (ያዕቆብ 2:21-26)

ሌላው ሁለቱ ክንፎችዋ ንጽሕናዎችዋ ናቸው፡፡ ዘንዶውን ንጽሕና ስለአላት አልተቋቋማትም፡፡ በዚህ ንጽሕናዋ አመለጠችው እንኳን የአምላክ ማደሪያ ንጽሕት መባል ሊያንሳት ሌሎች አማኞችም ንጹሐን እንደሚባሉ፤ “እንደ ንጽሕት ድንግል” (2ኛ ቆሮ 11:2) ተብሎ ተነግሯል፡፡ እመቤታችን በጸጋ ብቻ ሳይሆን በማኅጸንዋ በመሸከም የንጽሕና ማደሪያ ሆናለችና፣ ንጽሕና ያላት እናት ናት፡፡

እመቤታችን በውስጥ፣ በውጪም በሁለት ወገን ድንግል በመሆንዋ ሁለት ክንፍ ካለው ንስር ጋር ተነጻጽራ በመቀመጥዋ፤ በአሳብዋ ድንግል ለመሆንዋ “ወንድ አላውቅም” በአሳቤም የለም፣ እንዴት ይሆንልኛል በማለትዋ ታውቋል፤ በሥጋዋም ድንግል ስለሆነች፣ ከመውለድዋ በፊት ድንግል፣ በወለደች ጊዜ ድንግል፣ ከወለደች በኋላ በድንግል የኖረች ማሕፀንዋ “ተዘግቶ ይኖራል” ሰውም አይገባበትም በሚለው ትንቢት ያወቅናት፤ ይህቺ ሴት ድንግል ማርያም ብቻ ናት፡፡ (ሕዝ 44፡1-2)

እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ (ራእይ 12፡15)

እባብ እያለ የሚናገረው፣ በቀጥታ እባብ አይደለም፤ ይህ በእግዚአብሔር መጽሐፍ አገላለጽ የተለመደ ነው፡፡ “እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥” (ማቴ 23:33) በሚለው ውስጥ እናንተ እባቦች ያላቸው በተንኮል የሚታወቁትን ሰዎችን እንጂ የተፈጥሮ እባቦችን አይደለም፡፡ ስለዚህም እባብ ያለው ጌታ ሲወለድ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ነው፡፡ “ጌታ ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ . . .ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ” (ማቴ 2፡1-8)

“ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ” (ማቴ 2፡16) እባቡ ሄሮድስ ይህን ያደረገው ከሚገደሉት ሕፃናት መካከል አንዱ ይሆናል በማለት በመገመት ለወታደሮቹ ልኮ ሕፃኑን ለመግደል መሞከሩ ነበረ፡፡

ወንዝ የሚያህል ውኃ የተባለው ለወታደሮቹ የተተላለፈው ትእዛዝና የሠራዊት ብዛት በቤተ ልሔም መሠማራቱ ሕፃኑንና እናቱን ለመግደል የተተላለፈው ትእዛዝ ነው፡፡

ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው (ራእይ 12፡16)

ዮሴፍና ድንግል ማርያም ቤተ ልሔም ተቀምጠው ሳሉ ሄሮድስ መጥቶ እንዳያጠፋቸው ከሄሮድስ የተላለፈውን ትእዛዝ እንዳይፈጸም የጌታ መልአክ ተንኮሉን በመንገር እንደረዳቸው ለማመልከት ምድሪቱ ረዳቻት በማለት ተናገረ “የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው” (ማቴ 2፡13)

ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ (ራእይ 12፡17)

ዘንዶው በእርስዋ ላይ ለምን ተቆጣ?

: ከግዛቱ ከሲኦል ነፍሳትን የሚነጥቀውን ልጅ ወለደችበት

ዘንዶው ለ5500 ዘመናት የሰውን ዘር በሲኦል ሲቀጣ ኖሮአል፡፡ ነገር ግን አምላክ አንዲት ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያምን አስቀረለን፣ ከእርስዋም ሥጋን ተዋሐደ፡፡ ለዚህ ነው በትንቢት “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር” (ኢሳ 1፡9) ያለው፡፡

: ከጨለማ የሚያወጣውን ልጅ ስለ ወለደችበት ተቆጣ

ዘንዶው ለ5500 ዘመናት በጨለማ ሲገዛ ነበረ፡፡ እመ ብርሃን (የብርሃን እናት) ስትመጣ ግን “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው” (ኢሳ 9፡2) ይህን “የዓለም ብርሃን” (ዮሐ 8፡12) የሆነ ጌታ መጥቶ የጨለማውን ገዢ አስወገደው፤ “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን” (ቆላስይስ 1:13) ስለዚህ ከእርስዋ ባይወለድ ኖሮ አያሸንፈኝም ነበረ ብሎ አስቧልና ተቆጣት፡፡ ስለዚህም እስከ አሁን ድንግል ማርያምን የሚሳደቡ ለምን ከጨለማ በእርስዋ ሥጋ ነሥቶ አወጣን በማለት ሳያውቁም ሆነ አውቀው ክብርዋን የማይናገሩ ስለሆነ ሐዋርያው ይሁዳ ስለ እነርሱ “እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ፡፡ . . .ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት” (ይሁዳ 13) ይላቸዋል፡፡

: የሰው ልጆች ሁሉ ሊያጠፉ ነበረ፣ ነገር ግን መድኃኔ ዓለምን ወለደችበት

“ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና…ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ” (ሉቃ 2፡11) ሰዎች መድኃኒታቸውን ያገኙት ከእርስዋ ጋር ነው፡፡ ሰይጣን ግን ሰዎች እንዲድኑ እንደማይፈልግ እንዲህ ተጽፎአል “ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል” (ሉቃስ 8፡12) ባጠቃላይ ሰይጣን ዓለምን ከእርስዋ ተወልዶ ስላዳናቸው በእርስዋ ላይ ተቆጥቶአልና ልብ አድርጉ አንድ መናፍቅ መጥቶ ስለ ድንግል ማርያም ስትናገሩ ከተቆጣና ከተቃወመ የተቆጣው የዲያብሎስ ወገን መሆኑን አስተውሉ፡፡

ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ (ራእይ 12፡17)

ከዘርዋ የቀሩት ለጊዜው በዘር እስራኤላዊ የሆኑ 144 ሺህ ሕፃናት ናቸው፡፡ “ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ” (ማቴ 2፡16) እነዚህ ሕፃናት ንጽሕና ያልጎደፈባቸው ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ልጅ ለበጉ በኩራት የሆኑና ለእግዚአብሔር መንግሥት ተዋጅተውአሁን በዙፋኑ ፊት ሌትና ቀን ሲያመሰግኑት የሚኖሩ ሆነዋል፡፡ “አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም፣ የመንፈስ ቅዱስም ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ… .ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው፡፡ በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም” (ራእይ 14፡1-5)

የቤተ ልሔም ሕፃናት መሆናቸው የሚተታወቀው፡- “ከሴቶች ጋር ያልረከሱ”፤ “ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት”፤ “በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም” የሚሉት አባባሎች ናቸው፡፡ ሕፃናቱ ከሁለት ዓመት በታች ስለሆኑ ድንግል ናቸው፣ ውሸት አያውቁም፣ ነውር የሆነ ኃጢአት አልሠሩም እኒህን በኩር የተባሉ መጀመሪያ ከበጉ ክርስቶስ በፊት ለሰማዕትነት የተዋጁ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ዘንዶው ሄሮድስ ሕፃናቱን የሚገድለው ንጉሥ ክርስቶስ ከእነርሱ መካከል ይሆናል በማለት ስለሆነ ለበጉ ሲሉ የተዋጁትን ሊዋጋቸው መሄዱን በራእይ ተገለጸ፡፡

ሌላው ከዘርዋ የቀሩት እኛ ምእመናን ነን፡፡ ከመስቀል ስር የተረከብናት እናታችን ናት፡፡ ወንጌል ለሐዋርያት በመሰጠቱ ለእኛ አልተሰጠንም እንደማንል ሁሉ፤ ለቅዱስ ዮሐንስም እናት እንድትሆነው ስትሰጥ ለእኛም እናታችን ሆናለች (ዮሐ 19፡26)፡፡ ፈጣሪ አስቀድሞ ለእናትነት የመረጣትና የመሠረታት፤ መሠረተ ሕይወት ድንግል ማርያም የሰው ልጆች ሁሉ እናት ናት፡፡ በትንቢት “ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት” ይላታል (መዝ 86፡5)፡፡ እናት የተባለችው ጽዮን ድንግል ማርያም ለመሆንዋ አስቀድሞ ኢሳይያስ ዘር ባያስቀርንል እንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ቃል ጠቅሶ አስተምሮበታል (ሮሜ 9፡29)፡፡ “እነሆ፥ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዓለት አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም”(ሮሜ 9፡32-33) ብሎአል፡፡ ድንጋዩ (ዐለቱ) ክርስቶስ ነው (ኤፌ 2:20) ስለዚህ በድንጋይ የተመሰለው ክርስቶስ በየት ኖረ? ብንል በጽዮን ይለናል፡፡ ባጠቃላይ ጌታ ለእናትነት የመረጣት ጽዮን የሰው ሁሉ የጸጋ እናት ስለ ሆነች ዘሮችዋን እኛን አሁን ዘንዶው እየተዋጋን ነው፡፡ ማርያም ማርያም አትበሉ ይለናል፡፡ ዘንዶው ስሟ ሲጠራ ስለ እርስዋ ድምጽ ሲሰማ ይቆጣል፡፡ እኛ ልጆችዋ ግን ድምጽዋን ስንሰማ በደስታ ዮሐንስ መጥምቁ በማኅፀን ሳለ በደስታ እንደዘለለ እንዘላለን፣ እንደሰታለን (ሉቃ 1፡41)፡፡ ዘንዶው ይሰድባታል፣ ጠላቷ ነውና፤ እኛ ደግሞ ትውልድ በመሆናችን ልጆችዋ ነንና እናመሰግናታለን “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል` ብላናለችና እንታዘዛታለን (ሉቃ 1፡48)፡፡

አመስግነናት፣ ወድደናት፣ እናቴ ብለናት፤ እናት ለልጆችዋ የምታወርሰውን አዲሲቷን ምድር መንግሥተ ሰማያትን (ራእይ 21፡1-2) በአማላጅነትዋ በአባትዋ በዳዊት ትንቢት መሠረት “በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥ በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፡፡ ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ” (መዝ 44 (45)፡16-17) እንዳለው ስምዋን አሳስበን አዲሲቷን ምድር እንድታወርሰን የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁንልን፡፡

በአማላጅነትዋም ዘወትር አትለየን ምስጋናችንን ውዳሴያችንን ትቀበለን
“ሰዓሊ ለነ ቅድስት”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

Advertisements

“የድንግል ማርያም ልጅ” ነው ወደ ሰማይ ያረገው

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይሁንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ኃጢአት ሲል የተሰቀለው በሥጋው ነው፣ የሞተውም በሥጋው ነው፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣው በሥጋው ሲሆን፣ ወደ ሰማይ ያረገውም በሥጋው ነው፡፡

በዚህ ዘመን ያሉ ሐሰተኛ ወገኖቻችን መካከል፤ ጥቂቱ በሥጋው አልሰቀሉትም ሲሉን፤ ከፊሉ ደግሞ በሥጋውስ ተሰቅሎአል፣ ነገር ግን የቀብሩ ቦታ ሥጋው ስለ ጠፋ የተነሣው መንፈሱ ነው ይሉናል፤ ይህ ደግሞ ሠርቀውታል ከሚለው ከአይሁድ ሐሰተኛ ስብከት የማይተናነሥ ነው፡፡ ስለሆነም ከእነዚህ ሐሰተኞች ልንርቅ ይገባናል፡፡ ክርስቶስ የሚሰቀለው በሥጋው፤ የሞተው በሥጋው፤ የተነሣው በሥጋው፤ እንዲሁም ወደ ሰማይ ያረገው በሥጋው ነውና፡፡

– “ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው…እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር” (ዮሐ 2፡19-21)
– “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” (ዮሐ 3፡14-15)
– “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል፡፡ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፥ ይዘብቱበትማል ያንገላቱትማል ይተፉበትማል፤ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል” (ሉቃስ 18፡31-33)
– “የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ” (ሉቃስ 24፡6-7)

እነዚህ ጥቅሶች የሚያስረዱት የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ እንደተሰቀለልን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡ የሞተውም እንዲሁ በሥጋ መሆኑንና የተነሣውም በመለኮቱ (በመንፈሱ) ኃይል እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ያስረዱናል፡-

– “ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ” (1ኛ ጴጥ 4፡1)
– “መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም” (1ኛ ቆሮ 15፡3)
– “ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” (1ኛ ጴጥ 3፡18)

በአምላክ የሕይወት ቃሎች እንደምንረዳው በሥጋ የሞተው ክርስቶስ በመለኮት ኃይል፣ በአምላክነቱና በሁሉን ቻይነቱ ከሙታን ተለይቶ ሕያው ሆኖ የታየው ክርስቶስ በዚያው ሥጋ ተቀብሮ በዚያው ሥጋ እንደተነሣ እንድናምን ይረዱናል፡፡ ከሃይማኖታችን የወጡ ወገኖች ግን “በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” የሚለውን ቃል ይዘው በመንፈስ ነው የተነሣው ወደ ማለት አዘንብለዋል፡፡ ይህ በመንፈስ ተነሣ የሚል አመለካከት በሐዋርያትም ተፈጥሮባቸው በነበረበት ጊዜ ራሱ ጌታ እንጂ ሌላ መንፈሳዊ ፍጡር እንዳልሆነ ምላሽ ሰጥቶአቸዋል፡፡ “ጌታ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው፡፡ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው፡፡ እርሱም፦ ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው፡፡” ከዚህ ከጌታ ቃል “መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም” የሚለው በመንፈስ እንዳልተነሣ ሲያመለክት “እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ” የሚለው ደግሞ ራሱ የተሰቀለውና የሞተው እንደተነሣ ያስገነዝበናል፡፡ በራሱ ሥጋ እንደተነሣ የሚያስተምሩን ተጨማሪ ጥቅሶችን ይመልከቱ፡-

– ሴቶቹ ወደ መቃብሩ የመጡት ማንን ፈልገው ነው? የተሰቀለውን ሥጋውን፣ ምኑን ሽቱ ሊቀቡት ነው የመጡት? ሥጋውን፣ መልአኩ የተኛበትን ሥፍራ እዩ ከዚህ የለም ያላቸው ምኑን ነው? ሥጋውን ነው፡፡ “መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፡፡ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ” (ማቴ 28፡5-6)
– “የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ” (ማር 16፡6)
– ከተነሣም በኋላ ሲገለጥላቸው ከተናገራቸው ንግግር ማስተዋል የምንችለው ነገር አለን፡- “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸውበዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፡፡ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል” (ሉቃስ 24፡44-46) በዚህ ውስጥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ የሚለውን ስናጤነው፣ በምንድን ነበር፣ ከእነርሱ ጋር የነበረው? በሥጋ ስለሆነ፤ አሁንም የሚናገራቸው ያው የተነሣው ሥጋ መሆኑን አእምሮአችንን ከከፈትን ግልጽ የሆነ ቃል ነው፡፡
– ከተነሣ በኋላ የሚሰወረውና በዝግ ቤት የሚገባው መንፈስ ስለሆነ የሚመስላቸው ደግሞ አንዳንዶች ስላሉ፤ ለዚህም መልስ መስጠት ይገባናል፡፡ ይህ የመሰወሩ ተአምር ድንቅ አድራጊነቱን ከሃሊነቱን ያሳያል እንጂ ረቂቅ ሆኖ መነሣቱን አያመለክትም፡፡ ምክንያቱም በሥጋም ሣለ ይህንኑ ተአምር እንደሚሠራ “የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው” ይላል ይህ ሳይሞትም በፊት ያደረገው ተአምር ነውና አምላክነቱም የሚያመለክት ብቻ ነው (ዮሐ 12፡36)፡፡ ስለሆነም በሥጋ የተነሣው የሰው ልጅ (የድንግል ማርያም ልጅ) ያው እርሱ ተአምር አድራጊ መሆኑን የሚያስገነዝበን ነው፡፡

በዚሁም አንጻር የሞተውና የተነሣው በሥጋ እንደሆነ ሁሉ ወደ ሰማይም ያረገው የሰው ልጅ ኢየሱስ ከርስቶስ በሥጋው ነው፡፡ ይህንን ገና ወደ ሰማይ ወጥቶ በሥጋ በዙፋኑ እንደሚኖር የተተነበዩ ትንቢቶች አሉ፡፡

አዳም የፈለገው ከሥላሴ እንደ አንዱ ሆኖ በአምላክነት መኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለተኛው አዳም ሥጋን ለበሶ ከሦስቱ እንደ አንዱ የአምላክነት ሥልጣን እንደሚያገኝ እንዲህ ተጽፎአል፡- “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” (ዘፍ 3፡22)፡፡ ይህም “አዳም” የሔዋንን ባል እንዳልሆነ የምናስተውልበት ምክንያት አዳም ፍሬውን በመብላቱ ምክንያን እንኳን መልካምንና ክፉን ሊያውቅ የሞት ቅጣት ደርሶበታል “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” (ዘፍ 2፡17) የሚለው ሁሉን ታውቃለህ ሳይሆን ብትበላ ሞትን ትሞታለህ ነው፡፡

ታዲያ “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው እንዴት ነው የተፈጸመው ቢባል፤ በሁለተኛው አዳም ነው፡፡ “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” (1ኛ ቆሮ 15፡45) ስለሚል ኋለኛው አዳም መልካምንና ክፉን ያውቃል፤ ይህም ከእኛ ከተባሉት ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ እንደ አንዱ የሆነው የሰው ልጅ ክርስቶስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ወደ ሰማይ ያረገውና በዙፋኑ የተቀመጠው ወልድ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ብሎ አምላክ ትንቢት የተናገረው፡፡

“አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ” (መዝ 46/47/፡5) የሚለው እና “ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?” (ምሳሌ 30፡4) ላይ ያለው የእግዚአብሔር ልጅ የተባለው የድንግል ማርያም ልጅ ወደ ሰማይ ማረጉን አስቀድሞ መነገሩን ያስታውቀናል፡፡

“ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ 3፡13) በዚህ ቃል ውስጥ “ሰማይ” የሚለው ቃል ጠፈርን አይወክልም በትንቢተ ኢሳይያስ 66፡1 “ሰማይ ዙፋኔ ነው” በማለቱ ይህ “ሰማይ” ተብሎ የተነገረው “ዙፋን” የሚለውን ነው፡፡ በመሆኑን ጥቅሱ በማነጻጸር ስንተካው እንዲህ ይሆናል፡-

“ከዙፋኑም ከወረደ በቀር ወደ ዙፋን የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በዙፋን የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ 3፡13) የሚለውን ስለሆነ አሁን በዙፋኑ ያለው የድንግል ማርያም ልጅ እርሱም “የሰው ልጅ ነው” የተባለው ነው፡፡ ይህም እንዲታወቅ “በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ” (ራእይ 5፡13) በማለቱ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው በጉ እንዲህ ሲመሰገን የሚኖረው ወደ ሰማይ የወጣው ስለ እኛ የተሰቀለው ራሱ ክርስቶስ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ” (1ኛ ጴጥ 3፡22) ያለው፡፡

በሥጋ አልወጣም ለሚሉን መጽሐፍ ቅዱስን አለማንበባቸውን ያስገነዝበናል እንጂ የድንግል ማርይም ልጅ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ “ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ” (ማር 16፡19) በማለቱ ዐረገ የተባለው ኢየሱስ ነው፡፡ ይህ ስም ደግሞ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ የተሰጠው ስም ነው፡፡ “ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴ 1፡21) የተባለው ያው በሥጋ የተወለደውና በሥጋዌ ስሙ በሚጠራበት ስሙ በዚያው ኢየሱስ ተብሎ እየተጠራ ነው ወደ ሰማይ የሄደው “ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ” (ሉቃስ 24፡51) በዚህን ጊዜ ነው በሥጋ ከሞት መነሣቱን መላእክት እንዳበሠሩት አሁንም በዕርገቱ ጊዜ “እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፡፡ እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (ሐዋ 1፡9-11)፡፡

“ይህን የሚመሰክር። አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡”
(ራእይ 22፡20-21)

የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ (ቃና ዘገሊላ)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

“የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ”
(ቃና ዘገሊላ)

የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ የሚለው ትእዛዝ ሥልጣን ካለው አካል ቢነገር ውጤታማ ሲሆን፤ ሥልጣን ከሌለው ሰው ቢነገር ሰሚ ያጣ ነበር፤ ነገር ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ባለ ሞገስ፣ ባለ ጸጋ እመቤት በመሆንዋ ድምጽዋ (ቃልዋ) ተሰሚነት ያለው በመሆኑ አድርጉ በማለት ለአገልጋዮች ትእዛዝ አስተላልፋለች፡፡

ይህ ቦታ ቃና ዘገሊላ (ከገሊላ አውራጃ አንዷ ቃና) በተባለ ቦታ ነው፡፡ ዶኪማስ ሰርጉን ባደረገበት ወቅት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጠራት፡፡ በአገራቸው ልማድ ወላጅ ከተጠራ፣ ልጅ አብሮ ይመጣል፡፤ ልጅ መምህር ከሆነ ደቀ መዛሙርቱን ጠቅላላ ይዞ ነው የሚመጣው ስለዚህም ሁሉም በቦታው ታድመዋል፡፡

ከሰው ብዛት የተነሣ ተጠምቆ የነበረው የወይን ጠጅ ግን ሳይታሰብ አልቆአል፡፡ አገልጋዮች ወደ ወይን ጠጅ ክፍል ይገባሉ፤ ነገር ግን ይዘው የሚመጡት የወይን ጠጅ የለም፡፡ የሚጨንቅ ሰዓት ነው፡፡ ሰውን ሰርግ ጠርቶ የሚበላ ወይም የሚጠጣ የለም ማለት አሳፋሪ ነው፡፡

እመቤታችን “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው”፣ “በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻል” የሚባሉትን ሞገስ ያላት መሆንዋን ሕዝቡ አያውቅም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እርስዋ የማን እናት መሆንዋንም ጭምር የተገነዘበ የለም፡፡ ባለ ተአምራት ልጅ እንዳላት ያመነ፣ ሁሉን ካለ መኖር ወደመኖር ያመጣ ፈጣሪ እንደወለደች ከጥቂቶች በስተቀር በሠርጉ ያሉት ሁሉ አያውቁም፤ ደቀ መዛሙርቱ እንኳ እንዲያምኑበት የቻሉት ይህን የምልክቶች መጀመሪያ ካደረገ በኋላ ነው በእርሱ የአመኑት (ዮሐ 2፡11)፡፡ ስለዚህ አማልጅኝ፣ ጠይቂልኝ፣ ብሎ የሚለምናት አይኖርም፡፡ ባለ “ጸጋ” መሆንዋን አያውቁምና፡፡

ሁሉም የሚያውቁት ግን አንድ ነገር አለ፡፡ “እናት” ናት፡፡ እመቤታችን ጌታችንን የወለደችው በአሥራ ስድስት ዓመትዋ ነው፡፡ ጌታ ተወልዶ ሰላሣ ዓመት አልፎታል፡፡ ስለዚህም እርስዋ አሁን የአርባ ስድስት ዓመት እመቤት ናት፡፡ እስራኤላውያን “እናት” የሆነችን ማክበር ዕድሜ የሚያረዝም፣ ተስፋ ያለው መሆኑን አጥብቀው ይረዳሉ “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት” (ኤፌ 6፡2-3)፡፡

ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አገልጋዮቹን በመጥራት “የሚላችሁን አድርጉ” በማለትዋ፤ እነርሱ የሚታዘዝዋት ዕድሜያቸው እንዲረዝም ካላቸው መልካም ምኞት ነው ማለት እንችላለን፡፡ ከዚሁም ጋር አስተዳደጋቸው የእናት ትእዛዝ ንቆና ትቶ መሄድ የማይሞክሩት አይደለም፡፡ እመቤታችን የአርባ አምስት ዓመት እናት በመሆንዋ “እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” (ምሳሌ 23፡22) የሚለውን ትእዛዝ ንቆ እንደመሄድ ስለሆነ ምንም ይሁን የምታዛቸውን ለማድረግ ፍቃደኞች መሆናቸውን መገመት አያዳግትም፡፡

ድንግል ማርያም ዶኪማስ በሰርግ እንዲያፍር አልፈለገችም፡፡ በተሰጣት ጸጋ ወይን ጠጅ እያለቀ መሆኑን አውቃለች፡፡ ርኅርኅት በመሆንዋ እና ሁሉን ማድረግ የሚችለውን የእግዚአብሔርን ቃል በመውለድዋና ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነሥቶ ከእርስዋ ጋር አማኑኤል (እግዚአብሔር ራሱ) ተቀምጦ፤ ስለ ጭንቀታቸው ዝም ማለት አልፈለገችም፡፡ ስለዚህም ለምልጃ ወደ ፈጣሪዋ ቀረብ ብላ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው፡፡

የፈጣሪዋ መልስ ምንኛ በሚያስደስት ቃላት የተዋቡ ናቸው!፡፡ አንቺ “ሴት” በማለት አዳም ሔዋን ከእርሱ የተካፈለችውን አጥንትና ሥጋ ሊያስታውስ “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ያለውን ተናግሮ አጥንቴ ከአጥንትሽ ነው፤ ሥጋዬም ከሥጋሽ ነው የተገኘው አላት፡፡ እውነትም ድንቅ ነው፡፡

ቀጥል አደረገና ያልሽኝን ላላደርግልሽ፣ የምታዢኝን ላልፈጽምልሽ እንዴት እንቢ እላለሁ በማለት “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” የሚል የባህላቸውን ንግግር ተናገረ፡፡ ይህ አነጋገር ምን ጠብ አለን? የሚል የእስራኤላውያን የተለመደ አነጋገር ለመሆኑ ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች ብትመለከቱ በቂ ነው (2ኛ ሳሙ 19፡22፣ 1ኛ ነገሥ 17፡18፣ 2ኛ ነገሥ 3፡13፣ ማር 5፡7፣ ሉቃ 8፡28)፡፡

ሁሉን አዋቂ የሆነው አምላካችን ኢየሱስ፣ ከእናቱ ጋር የመጣበት፣ የራሱ የሆነ ምክንያት አለው፡፡ እንዲያው ለከንቱ አይደለም፡፡ ስለዚህ የለመነችውን ልመና ሊያደርግላት ጥቂት ጠብቂኝ ለማለት “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት፡፡ እርሱ በአንድም በሌላም ቢናገርም ለተነሣንበት ርዕስ ለመማር በወቅቱ ወይን ጠጁ በድንጋይ ጋኖቹ ውስጥ ሙጥጥ…. ብሎ አላለቀም፡፡ እነርሱ ማለቅ አለባቸው፡፡ የዚህም መሟጠጥ ትልቅ ምክንያት አለው፡፡

ባልተሟጠጠ የወይን ጠጅ ላይ ውኃ ጨምሮ ተአምር ቢሠራ አምላካችን አይደነቅም፣ ለአምላክነቱም ገላጭ አይሆንም ነበር፡፡ ይህንን ነቢያትም ይሠሩታልና፡፡ ነቢዩ ኤልሣዕ በዕዳ ለተያዘች ሴት በቤትዋ ያለውን የዘይት ማሰሮ አበርክቶላት ከጐረቤቶችዋ በሰበሰበችው ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን እያንጣፈፈች በመሙላት አበርክቶ ተአምር እንደ ሠራላት እስራኤል ሁሉ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ጌታም እንዲሁ ጥቂቱን ወይን ጠጅ ቢያበረክት እንደ ነቢይ ከመቁጠር ውጪ ሊያደንቁትና ሊያምኑበት አይችሉምና ጥቂት ጊዜ እንድትጠብቅና ያለችውን እንደሚያደርግላት ነገራት፣ በዚህም እጅግ አስደሰታት፡፡

ከደስታዋ የተነሣም ጊዜው ሲደርስ ወይኑ ተሟጥጦ በነበረበት ወቅት እናታችን እመቤታችን ለአገልጋዮቹ የሚላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አዘዘቻቸው፡፡ እርስዋ ሳታዝዛቸው፤ ራሱ ጌታ ጠርቶ “የምላችሁን አድርጉ” ቢላቸው ኖሮ ምን እንደሚፈጠር መገመት አያዳግትም፡፡

ጌታ በዚህ ጊዜ ሰላሣ ዓመቱ ነው፤ አስተናጋጆቹ ደግሞ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት እርሱ በሕዝብ ሁሉ ፊት ተአምር አድርጎ አያውቅም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለን “ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ” በማለቱ በሕዝቡ እውቅና ባለማግኘቱ ወጣቶቹን የሠላሳ ዓመት እኩያቸው ቢያዛቸው፤ ምናልባትም ወይን ጠጅ በማለቁ ምክንያት፣ ተናድደው ባሉበት ሰዓት ውኃ ቅዱ ቢላቸው፣ በእኩያነታቸው አልታዘዝ ብለው ለተአምሩ እንቅፋት ሊሆኑ ይችሉ ነበር፤ በሰው ሰውኛ አሁን ቀድቶ አሁን ጠምቆ ወይን መሥራት አይቻልምና፡፡

ነገር ግን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ያለቻቸው “እናት” ናት፡፡ “የእናትህንም ሕግ አትተው” (ምሳሌ 6፡20) የሚለውን አጥብቀው የሚከተሉ አማኞች ስለሆኑ፤ ምንም አሥራ ሁለት እንስራ ወይም አስራ ስምንት እንሥራ ያህል ወንዝ ወርደው ከምንጭ ቀድተው መሙላት በእነርሱ “ምን ሊያደርግ ይሆን” የሚል ጥያቄ በአእምሮአቸው ቢመላለስም ቃሉ “የእናትህንም ሕግ አትተው” ስለሚል በእናቱ ትእዛዝ መሠረት አምላካችን ክርስቶስ ያላቸውን ሁሉ ያውም እስከ አፍ ገደፋቸው ድረስ በመሙላት ከብዙ ድካም በኋላ ፈጽመዋል፡፡

የዚህ ሁሉ የመታዘዛቸው ውጤት ምንድን ይሆን? አሁንም ሌላ የሚላቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ በአምላካዊ ሥልጣኑ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ የቀየረበትን ተአምሩን ከፈጸመ በኋላ፤ ቀጠሎ ሌላ ትእዛዝ “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት” አላቸው፡፡ ሲቀዱት ምን ያህል ያስፈነድቃቸው?፣ ምን ያህል እየፈጠኑ ለአሳዳሪው እንዲቀምሰው ሮጠው ይሰጡት?፣ ድንቅ አድራጊውን ጌታ ላይ ዓይናቸውን ሳይነቅሉ፤ በደስታ ይመለከቱታል፡፡ ይህን ያደረገ እርሱ መሆኑን የሚያውቁት አገልጋዮቹ ናቸውና፡፡ ጭንቀታቸው ያቃለለችው፣ ትእዛዟን በማክበራቸው ደስታ አግኝተዋል፡፡ አልታዘዛትም ቢሉ ኖሮ የሚያጡት ይህንን ደስታ ነበርና፡፡

የመታዘዛቸውን ውጤት አሳዳሪው በመቅመስ የሙሽራው ወይን መስሎት በማድነቅ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።”

በፍጹም ሙሽራው አልጠመቀውም፡፡ የእርሱም አይደለም፡፡ የድንግል ማርያም የምልጃ ውጤት፣ የአገልጋዮቹ የመታዘዝ ትጋት፣ ዕንቁ የሆነው የአዳኛችን፣ የፈጣሪያችን፣ የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር ነው፡፡

ቃና ዘገሊላ ለሕዝብ ሁሉ በመጀመሪያ ጊዜ ድንቅ ሥራ ተፈጸመባት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት ታወቀባት፣ የእግዚአብሔር ወልድ ኤልሻዳይነት ተመሰከረባት፣ የደቀ መዛሙርቱ እምነት ተጀመረባት፡፡

አሁን የእኛ ቃና ዘገሊላ ቤተ ክርስቲያናችን ናት፡፡ በዚያ ጌታ ሰርግ ጠርቶናል፣ በዚያም እናቱ በአማላጅነት አለች፣ ሐዋርያት በቅዳሴው ይታደማሉ፣ ስቡህ፣ እኩት፣ ውዱስ ቅዱስ ይላሉ፤ ካህናት ቅዳሴውን ጀምረው ለዓለም የሚሆን ሥጋ ወደሙን ለመፈተት፣ ከሕዝቡ ጋር “እግዚኦ፣ እግዚኦ” እያሉ ጌታን ይለምኑታል፡፡ እርሱም የቀረበውን ኅብስት እና ወይን፤ ወደ ሥጋውና ደሙ ይቀይራል፡፡ “ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ” ተብለናልና ንስሐ ገብተን ጸድተን ወደ ክርስቶስ ሥጋውና ደም እንቅረብ፡፡ ለዚህም እመቤታችን በአማላጅነትዋ አትለየን፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእናቱን ልመና ሰምቶ ለመንግሥቱ የበቃን ያድርገን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የልደትን በዓል ደስታ የትና በምን ይሁን???

የልደትን በዓል ደስታ የትና በምን ይሁን???

የሰው ሕይወት ያለ እግዚአብሔር ደስታ አያገኝም፤ እግዚአብሔር የሌለው ሰው በውስጡ ሰላምና ደስታ አይሰማውም፡፡ በበዓል ቀን በሥጋ ደስታ ለማግኘት የሚሻ ሁሉ ይበላል ይጠጣል፣ ግን አይረካም፤ ይለብሳል፣ ግን አይደምቅም፤ ይሮጣል፣ ግን ማንንም አይቀድምም፣ ደመወዝ ይቀበላል፣ ግን በማይረባ ጉዳይ ሲዘራው ይውላል (ሐጌ 1፡5-6)፤ በበዓል የተመኘውን ሁሉ ለማድረግ ይጣደፋል፤ ያለ እግዚአብሔር ነውና በዚህ ሁሉ ደስታ የለውም፤ እንደው ሰክሮ ሲጋጭ፣ ሲገጭ፣ ሲፈነከት ሲፈነክት ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ የደረሰበት በውስጡ እውነተኛው የደስታ ምንጭ ክርስቶስንና ሕጉን ስላልያዘ ነው፡፡

እግዚአብሔር የሌለበት ደስታ መጨረሻው ጥፋት ነው፡፡ በጌታችን ልደት ዕለት መላእክትና እረኞች ሲያመሰግኑ፤ በሄሮድስ ቤተ መንግሥት ግን የጥፋት ሸንጎ ተይዞ ጌታን ስለመግደል ይዶለት ነበር፤ እንዲሁ ዛሬም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የልደትን በዓል በዝማሬና በቅዳሴ ሲያከብሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ በመንፈሳዊ በዓል ስም፣ የዳንስ ምሽት አዘጋጅተው በመጨፈርና በመዳራት ጥፋታቸውን ያፋጥናሉ፡፡ ወገኔ የአንተ ደስታ “ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ” ከተባሉት ጋር የቅዳሴው ቦታ ይሁን (መዝ 41፡4)፡፡

በዘፈን ከሰይጣን ጋር ሆነህ ከምታመሽ፤ ንስሐ በመግባት ከእግዚአብሔር ጋር ሆነህ ስሙን ቀድሰህ፣ ሥጋውንና ደሙን በመቀበል፤ ያለምን ገንዘብ ማባከን ደስታን አግኝና፤ በዓሉን ከድሆች ጋር በመሆን፤ ለዘፈን የምታውለውን፣ ለዳንስ ምሽት የምትከፍለውን፣ ልብህ እስኪጠፋ ደስታ አገኝበታለሁ ብለህ የምትጨፍርበትን ገንዘብ እስቲ ለችግረኞች በመስጠት ደስታን እፈስበት፡፡ “የኃጢአተኛ …ደስታ ቅጽበት መሆኑን አታውቁምን?” (ኢዮብ 20፡5) ስለተባለ አንተ ለምን ለዚህ ኃላፊ ደስታ ትሠራለህ? ምንም ባለጸጋ ሁን በገንዘብህ መብትም ቢኖርህም ይህ “አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ” (ገላ 5፡13) መባልህ አስታውስና የተቸገረን ሰው ወደ ቤትህ ጠርተህ ከእርሱ ጋር በመዋል ስትደሰት ዋል፡፡

ደስታ የሚገኘው በመብል በመጠጥ ከሆነ፤ ተካፍለህ በመብላት ደስታን አግኝ፡፡ ራስን በመሳት ደስታን አገኛለሁ ብለህ በአልኮል መጠጥ ውስጥ ከምትደበቅ፤ ራሰህን ገዝተህ፣ በአእምሮ ሆነህ፣ ለድሆች በማሰብ እስቲ ደስታን ሸምት፡፡ ከዘፋኞች ጋር የምትስቀውን “ሳቅን፦ ዕብድ ነህ ደስታንም። ምን ታደርጋለህ?”ብለኸው (መክ 2፡2)፤ ከክርስቲያኖች ጋር የምትደሰተው ደስታ የጊዜያዊ ስላልሆነ “በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር” መሆንን ምረጥና የዘላለምን ደስታ በቅዳሴና በውዳሴ ሸለቆ ከክርስቲያን ወገኖችህ ጋር ተሻማ (ዕብራ11፡25-26)፡፡

እኛ የክርስቶስ ነን ያልን ክርስቲያኖች ሁሉ፣ የጌታችንን ልደት ስናከብር፤ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላም፣ ራስን ለሌላው አሳልፎ መስጠትን በማሰብ ሊሆን ይገባል፡፡ የዛሬዋ ዓለማችን ሁሉም ለራሱ ጊዜያዊ ደስታ እንጂ የሌላውን ችግር የሚያይበት ዓይን የለውም፤ በመስገብገብ ነገ የሚያጣ ስለሚመስለው ሌላውን አይረዳም፣ በዚህም ይረገማል “ለድሀ የሚሰጥ አያጣም ዓይኖቹን የሚጨፍን ግን እጅግ ይረገማል” (ምሳ 28፡27) እኛ ግን ከዚህ ርግማን ለመዳን ልንረዳዳና ልንተያይ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ገንዘብ ሲሰጥህ በመጋቢነት ሥልጣን ድሆችን እንድትመግብለት ፈልጎ ነው (ሉቃ 12፡42)፡፡

እግዚአብሔር አልቆና አክብሮ የፈጠረውን ሰውነታቸውን አክብረው ሊከብሩበት ሲገባ፣ የተዘጋጀላቸውን ቅዱስ በዓልና የድኅነት መንገድ ሁሉ ለማይረባና ጨፍረውም ሆነ አብደው ለማይረኩበት የውጣቸውን ጉድለት እንደማደንዘዣነት ለሚጠቀሙበት ጊዜያዊ ስሜት የሚያውሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ያውም ቢሆን ስላመኑበት ብቻ ያደርጉታል እንጂ ሲረኩበት አይታዩም፡፡ እርካታ ለድሀ በማሰብ፤ አብሮ ተካፍሎ በመብላት ደስታ መገኘቱ ተረስቶአል፡፡ “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል” (መዝ 40፡1)፡፡

የልደትን በዓል በምናከብርበት ወቅት እንደ መላእክትና እረኞች አብረን በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን ሊሆን ይገባል፡፡ በበዓሉም ካጡትና ከተቸገሩት ጋር ቤተ ክርስቲያን በምታዘጋጀው የድሆች መግቦት ጋር እናክብረው፤ በራስ ወዳድነት እኔ ብቻ ልብላ ሳይሆን አብረን እንብላ የማለት መንፈስ ይታይብን፤ “የሚሰጥ በልግስና ይስጥ” (ሮም 12፡8) ያለውን ተግባራዊ በማድረግ በደስታ እየሰጠን በዓሉን ከድሆች ጋር አብረን ለማድረግ እናስብ፡፡ እኛ የበላነውን ፍርፋሪ እንኳ የሚመኙ ስንት ናቸው?፤ ለጊዜያዊ ደስታ አባክነነው ምግቡ ወደ ቆሻሻ ሲደፋ ድሆች በረሀብ ሲሰቃዩ፣ ኋላ ሞት አይቀርምና “አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ” ተብሎ ወደ መሰቃያ ቦታ ከመጣል ይልቅ አብረን መልካሙን ሁሉ ከድሆች ጋር በማድረግ ክርስቶስ ሲመጣ ብራብ አብልታችሁኛል፤ ብጠማ አጠጥታችሁኛል የሚለውን የሕይወት ቃል ሰምተን በመንግሥቱ መሰብሰብ ይሻለናል (ሉቃ 16፡25፣ ማቴ 25፡35)፡፡

ጌታችን በተወለደበት ዕለት ባዩት ብርሃን በሰሙት ብሥራት እረኞች በመደሰት ከመላእክት ጋር በአንድነት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብዕ” በማለት እንዳመሰገኑ እኛም በጌታ መወለድ በዓል ብቻ ሳይሆን በዚህች ምድር እንድንኖር በተሰጠን ዘመን ሁሉ፣ ከማይጠቅሙንና ደስታችንን ከሚያደፈርሱ የዓለም ምናምንቴ ዘፈኖች፣ መዳራቶችና ቧልቶች ርቀን፤ በዚህ ፈንታ ቤተ ክርስቲያን ባዘጋጀችው የሌሊት ቅዳሴ በመገኘት “በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤት ያድርጉ፥ በደስታም ደስ ይበላቸው” (መዝ 67፡3) ከተባሉት ጋር ስናመሰግን እንኑር፡፡

መላእክትና እረኞች ለምስጋና፤ ሰብዓ ሰገልን ስጦታ ለማቅረብ፤ እንስሳትን እስትንፋሳቸውን ለመገበር ያበቃ አምላክ የእኛንም የልብ ምስጋናችንን ቅዳሴው ባለበት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተን ደስታችን ከዘፋኞች ጋር ሳይሆን “ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር” ነውና የቅዳሴውን ዜማ እያዜምን ጌታችንን በማወደስ ነፍስና ሥጋችንን እናስደስት (ያዕ 5፡13)፤ በበዓሉም ቀን ከድሆች ጋር ተካፍለን በመብላት ከውስጥ የማይጠፋ ደስታን እንሸምት፤ ይህንን እንድናደርግ የደስታ ምንጭ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሁን፤ ልጅዋን ወልዳ ለዓለም ያበረከተች እመቤታችን ጸሎትዋ ይደረግልን፤ የልደቱ ረድኤትና በረከት ከሁላችን ጋር ይደር፡፡ አሜን!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መልአክ ይባርክህ

“መልአክ ይባርክህ”

እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ስለምናምን “መልአክ ይባርክህ”ብለን የመናገር ድፍረት አለን፣ መናፍቃን ግን “ቅዱስ ገብርኤል ይባርክህ” ማለትን ይፈራሉ፡፡

መናፍቅ ማለት ተጠራጣሪ፣ ከፍሎ አማኝ ማለት ነው፡፡ እኛ ከእኛ እምነት ውጪ ያሉትን በዚህ ስያሜ የምንጠራበት ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ አዋልድ ጽሑፎችን ስለማይቀበሉ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ ያለውንም ጭምር ከፍለው፣ የሚፈልጉትን ብቻ መርጠው ስለሚቀበሉና ያልተቀበሉትን ቃል “በሉት” “እመኑት” ሲባሉ ስለማያምኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-

ከመናፍቃን አንደበት የማትሰሙአቸው አምስት ነገሮች፤ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳት ጽሑፎችን የሚሉአቸውን በመጠኑ ላስጎብኛችሁ፡-

1. መናፍቃን “የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ይባርክህ” ብለው መናገር ኑፋቄ ስለሚመስላቸው አይሉም፣

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉት ቅዱሳን ሰዎች ያውም ጌታችን የሚኮራበትና እንደውም የማን አምላክ እንደሆነ ሲናገር “የያዕቆብም አምላክ ነኝ” የሚልለት ታላቁ እስራኤል የተባለ ያዕቆብ “ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ” (ዘፍ 48፡16) ብሎ መልአክ ልጆችን እንዲባርክ ተናግሮአል፡፡ አንድ መናፍቅ የእኛ ካህን “ቅዱስ ገብርኤል ይባርካችሁ” ሲል ቢሰሙ፤ ወይም ከድርሳናት ውስጥ ይህን ቃል ቢያገኙ፤ እንደ ኑፋቄ ቆጥረው፣ እኛን “መናፍቅ” ሲሉን ይገኛሉ፤ የአብዬን ወደ እምዬ ልጥፍ ማድረግ ልማዳቸው ነውና፣ የእነርሱን ኑፋቄ መሸፈኛ እኛን መናፍቅ ናችሁ በማለት ይደመድማሉ፡፡ ቀድመን እኛ መናፍቅ እንዳንላቸው የሚጥሩበት መንገድ ነው፡፡

2. መናፍቃን “የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ይጠብቅህ” ብለው መባረክ ይፈራሉ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህ እውነት ጽፎአል፡፡ ያውም የእውነት ምንጭ እግዚአብሔር ራሱ ለሕዝበ እስራኤል ሲነግራቸው “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ” (ዘጸ 23፥20) እያለ፤ እነርሱ ግን የሐሰት ምንጭ የዲያብሎስ መልእክተኞች ስለሆኑ፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይጠብቅህ ስንል ከሰሙ፤ “ከእግዚአብሔር ሌላ ጠባቂ የለም እንዴት እንዲህ ትላላችሁ?” በማለት የእነርሱን ኑፋቄ በእኛ ላይ ለማላከክ እኛኑ መናፍቃን ለማለት ይሽቀዳደማሉ፡፡ አሁን የእኛ ካህን ወይም ድርሳነ ገብርኤል ብሎት ቢሆን ይህ መጽሐፈ ኑፋቄ “መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይጠብቅሃል ይላል” በማለት ያጣጥሉት ነበር፤ ድርሳነ ገብርኤል ግን የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ልጅ በመሆኑ ተመሳሳይ አሳብ ያስቀምጣል፤ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና” (መዝ 90፥11) የሚለውን ገልብጦ የያዘ የኑፋቄ መጽሐፍ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ልጅ ነው፡፡

3. መናፍቃን “የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከክፉ ያድንህ” ብለው መናገር ያንቀጠቅጣቸዋል፡፡

በእነርሱ ሕሊና “መዳን በማንም የለም” የሚለው ቃል የምንሽር ስለሚመስላቸው፤ አንዱን ጥለው ሌላውን አንጠልጥለው በግማሽ ልብ መጽሐፍ ቅዱስን አቅፈው ይሄዳሉ፣ ግማሽ ልብ ማለት መናፍቅ ማለት ነው፡፡ ሰው በምድር ሳለ ክፉ ነገር ያጋጥመዋል፤ መናፍቃን ደግሞ መላእክት ከክፉ ሊያድኑን እንደተሰጡን አይቀበሉም፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ” (ዘፍ 48፥16) ብሎ በተግባር እንዳዳነው ሲናገር፤ እንዲሁም እኛ የእግዚአብሔር አዳኝነትን የምናምን ምእመናን “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” (መዝ 33፥7) ተብሎልናል፡፡ መናፍቃን ግን ከፍሎ አማኝ ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን እየቆራረጡ ስለሚቀበሉ፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከክፉ ያድንህ የሚለውን ያጣጥላሉ፡፡

4. መናፍቃን “ጸሎትህ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል እጅ ወደ እግዚአብሔር ይውጣልህ” ማለትን አጥብቀው ይጸየፋሉ፡፡

ትዕቢት ውጥር አድርጎ ስለያዛቸው፤ እኔው ራሴ እግዚአብሔርን አነጋግረዋለሁ እንጂ መልአኩ ምን አገባውና ነው እርሱ የእኔን ጸሎት ይዞ የሚወጣው በማለት እርዳታቸውን አይሹም፤ እርዳታቸውን የሚፈልግ ሰውም ካለ፣ እንደ መናፍቅ ይቆጥሩታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ሰዎች ሲጸልዩ ግን ከእግዚአብሔር ጋር እንኳ ሲነጋገሩ በትሕትና እንጂ፣ “እኔ በፊቱ ልቀርብ ይገባኛል” አይሉም፡፡ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” (ያዕቆብ 4፡6)፡፡

በፊቱ ስንጸልይ እንደ ጻድቁ አብርሃም በትሕትና “እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ” (ዘፍ 18፡27) እያልን ክርስቶስን ማረን እያልን በጸሎት ስንጠይቅ፣ እንደ ሙሴ “በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ” በማለት እነዚያ ጻድቃንን እንደጠሩት እንጠራለን፡፡ በዚህን ጊዜ “እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ” (ዘጸ 32፡13-14) እንዳለው በእነርሱ ቃል ኪዳን ይራራልናልና፡፡

መናፍቃኑ የመላእክቱ ጸሎት ማሳረግን በድርሳናት እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ያለ ስለማይመስላቸው፣ አንግበው የሚሄዱት መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ” (ራእይ 8፡3-4) ይላል፡፡ እኛም ጸሎታችንን ይዘው ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ይረዱናል ስንል መጽሐፍ ቅዱስን ተመልክተን ነው፤ እኛ የመላእክት ጸሎታችንን ይዘው መውጣትና ማሳረጋቸውን መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰን ያመንነውን “መናፍቅ” ካሉን፤ እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ያላመኑት፣ ምን ሊባሉ ነው? እየተጠራጠሩ የሚያጠራጥሩት መናፍቃን ሳይባሉ፤ መናፍቅነትን ወደ እኛ የሚወረውሩት መናፍቅ አይባሉም ይሆን?፣ ተንጋለው ቢተፉ ተመልሶ ከፉ ማለት ይህ ነው፡፡

5. መናፍቃን “መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ማራቸው ብሎ እግዚአብሔርን ይጠይቅልህ” ማለት አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ ሲባል ከሰሙ ደም ስራቸው ይገታተራል፡፡

እነርሱ ፈጣሪ ነው በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እንዲጸልይላቸው የሚፈልጉት፡፡ ፈጣሪ ፈጣሪን እንዲማልደው፣ በተጠመዘዘና በተጣመመ ቃል “የሚማልደው” ብለው አንዴ ስለደመደሙ፣ ፍጡር የሆነው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸሎት ሳይሆን ፈጣሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲለምንላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ወይ ጉድ በዙፋን ተቀምጦ የሚለምን ፈጣሪ አለ ብለው ማሰባቸው???

መልአኩ ገብርኤል ፍጡር ስለሆነ የእኛ መጥፋት ስለሚያሳስበው፣ ወደ ጌታ ፊት ቀርቦ “የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” እያለ ጸሎት ሲያደርግልን በዙፋኑ የተቀመጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ “በምሕረት ተመልሻለሁ” ብሎ መልስ እንደሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የመላእክት የጸሎት እርዳታቸው ወደ ምሕረት እንደሚያደርሰን ተጽፎ ሳለ መናፍቃኑ አይቀበሉትም (ዘካ 1፡12-16)፡፡

እኛ ኃጢአተኞች ስለሆንን ዕድሜ ለንስሐ እንድናገኝ፣ መልካምነት ሲጠፋብን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈራጅነቱ “ይቆረጥ” ብሎ ሲፈርድ፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን ቀርቦ “ይህችን ዓመት ደግሞ ተዋት” እያለ ይማልድልናል ስለዚህ የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ጸሎት ያስፈልገናል (ሉቃ 13፡6-9)፡፡ የጸለየውም ጸሎት ምላሽ አግኝቶ ንስሐ ስንገባ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እና ሌሎቹ መላእክት ከእርሱ ጋር አብረው ስለ እኛ ደስ ይላቸዋል (ሉቃ 15፡10)፡፡

ቅዱሳን መላእክት፣ እናንተን የሰጠን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነውና ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡ እናንተን መናቅ አታስፈልጉንም ማለት እግዚአብሔርን መናቅ ነውና፣ ይህንን የእናንተን እርዳታ መቀበል ኑፋቄ አድርገው ከሚሰብኩን ወገኖቻችን ልብ ሰጥታችሁ እነርሱንም ለንስሐ እንዲበቁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እንድትጸልዩላቸው ለእኛም የእናንተ ቃል ኪዳንና ጸሎት እንዲሁም እርዳታ ስለሚያስፈልገን ጸሎታችንና ጥበቃችሁ እርዳታችሁ አይለየን፡፡

መናፍቃን ይህን ብቻ ሳይሆን የሚሉት እኛ መላእክት ያማልዳሉ ስንል ለማምለክ ያሰብን አድርገው ይተቹናል፡፡ ያማልዳሉ ማለት ይጸልያሉ ማለት ሲሆን ይህም ፍጡራን ስለሆኑ ለሰው ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ ማለት ነው፡፡ “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል” (ዳን 12፡1) በተባለው መሠረት ስለእኛ ጉዳይ እንዲምረን ይቆሙልናል፡፡ ይህ የሚያሳየው ፍጡርነታቸው መናገር እንጂ አምላክ ናቸው ከሚል ጋር አይገናኝም፡፡

ባጠቃላይ አባታችን ያዕቆብም መልአክ ከክፉ እንዳዳነው ሲናገር ፕሮቴስታንት በሕይወታችሁ እንደዚህ እንደ ያዕቆብ “መልአክ ይባርክህ ብላችሁ ታውቃላችሁ?” ወይስ “መልአክ ከክፉ አዳነኝ” ብላችሁስ መስክራችሁ ታውቃላችሁ? ካላወቃችሁ፣ እንደ ያዕቆብና እንደ ዳዊት እኛ ጠብቀን፣ ከክፉ አድነን ስላልን ለምን ትወቅሱናላችሁ? እኛ እንዲህ በማለታችን ኑፋቄ ከሆነ፣ ከላይ ያሉት እነ ንጉሥ ዳዊትና አባታችን ያዕቆብም መናፍቃን ናቸው ልትሉን ነው? እነርሱ ትክክል ካልሆኑ ጥቅሱ ለምን ተጻፈልን? ለምንስ ይዛችሁት ትዞራላችሁ? ካላመናችሁበት ለእኛው ለቀቅ አድርጋችሁ ዞር ለምን አትሉም?

መናፍቃን ልብ ይስጣችሁ፣ አሜን!

የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወዳጆች፣

ቅዱስ ገብርኤል ይባርካችሁ፣
ቅዱስ ገብርኤል ይጠብቃችሁ፣
ቅዱስ ገብርኤል ከክፉ ያድናችሁ፣
ቅዱስ ገብርኤል ጸሎታችንና ምጽዋታችሁን ያሳርግላችሁ፣
ቅዱስ ገብርኤል በጌታ ፊት ቀርቦ ማራቸው ብሎ ይጸልይላችሁ፤ ምልጃውም ትድረስላችሁ፡፡ አሜን! አሜን! አሜን!

በበዓላት ቀን በመዝፈን ከጌታ ጋር አትጣሉ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

በበዓላት ቀን በመዝፈን ከጌታ ጋር አትጣሉ

ጽድቅ የሰፈነባትን፣ ድኅነትና የዘላለም ሕይወት የሚገኝባትን መንግሥተ ሰማያትን ሁላችን እንሻለን፡፡ ይህቺውም በጌታችን በአምላካችን፣ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተከፈተች የድኅነት መንገድ ናት፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ፈጣሪያችንን በማመንና በስሙ በመጠመቅ አንድ ጊዜ ይህቺን የዘላለም መንገድ እየተጓዝንባት እንገኛለን፡፡

ይህ የመንግሥተ ሰማያት በር የተከፈተው እንዲሁ በቀላሉ ሳይሆን በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ” ያለው (1ኛ ጴጥ 118-19)፡፡ አሁን በዚህ ውድ ልጁ ደም የተዋጀን ሁላችን የእርሱን ውለታ የምንመልሰው ባይሆንም፣ ፍቅራችንን የምንገልጽለት መንገድ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” (1ኛ ጴጥ 2:24) ተብሎአልና በጽድቅ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡

ፈጣሪያችን ከዲያብሎስ መዳፍ አላቆናል “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” (ቆላስ 1፡13-14) ከዚህ ከገባንበት መንገድ ሊያወጣን የሚችል ወጥመዶች ግን ተዘርግተውብናል፡፡ “በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋል” (1ኛ ጴጥ 3፡9) ተብለን ወደ መንግሥቱ የሚያስገባው ጥሪው ቢደርሰንም፣ ወደዚህ ሕይወት እንዳንገባ የሚያደርግ ሌላ እንቅፋት አለብን፡፡

ጥሪውን ሰምተን ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት የምንችለው፤ በጠሪው በእግዚአብሔር ፈቃድ ስንመላለስ እንደ ምክሩ ስንሄድ ብቻ ነው (1ኛ ተሰ 2፡11-12)፡፡ እግዚአብሔር ውድ ልጁን ለዓለም አንድ ጊዜ በመስቀል ሞቶ መንግሥቱ ከፍቶልናል፣ እኛም ይህን ፍቅር ቀምሰን አይተናል፤ ስለዚህ “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” (1ኛ ዮሐ 4፡19)፡፡ ነገር ግን ይህ ፍቅር የሚለካው እንደ ቃሉ ከሆነ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ 14፡15) ባለው ይረጋገጣል፡፡

እግዚአብሔር ደስ ለማሰኘት ምንም አይነት እርም ነገር ተሸክመን አንድንከተለው አያስፈልግም “በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኘውን ታደርግ ዘንድ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ስትሰማ፥ … እርም ከሆነው አንዳች ነገር በእጅህ አይንጠልጠልብህ” (ዘዳ 13፡17-18) ብሎናልና፡፡ አንጠልጥለን የምንከተለው ጸያፍ ነገር መኖር አይገባውም፡፡

ክርስቲያን የራሱን ደስታ ብቻ ሳይሆን፣ ፈጣሪን ምን ያስደስተዋል ብሎ በማስተዋል ይመለከታል፡፡ ለዚህ ነው ክቡር ዳዊት “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ” (መዝ 26፡4) ያለው፣ ፈጣሪን የሚያስደስተውን የሚያደርግ ደግሞ ከፈጣሪ ዘንድ ሁሉንም በረከት በመጨረሻም ያገኛል፡፡ “ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን” (1ኛ ዮሐ 3፡22) እንዳለ፡፡

መንግሥተ ሰማያትን የሚያስቀሩብን የሥጋ ፍላጎቶቻችን ናቸው፤ እነዚህም የሥጋ ፍላጎቶች በጎ ሥራዎች ሳይሆን ክፉ ምኞቶቻችን ሲሆኑ፣ ክርስቲያን ደግሞ “ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ” (1ኛ ተሰ 5፡22) የሚለውን መመሪያ መከተል አለበት፡፡ ክፉ የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስምና፡፡ “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል” (2ኛ ጢሞ 2፡22) የተባለው ከዚህ የተነሣ በመሆኑ ማናቸውንም የሥጋ ሥራ ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡

መንግሥተ ሰማያት ከሚያስቀር ጥቂት ከሚባል አናሣ የሥጋ ሥራም ቢሆን መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ጥቃቅን የምንላቸው የኃጢአት አይነቶችም ቢሆን በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናቸውና፡፡ እግዚአብሔር ጥቂት የኃጢአት እርሾ እንኳ እንዲኖርብን አይፈልግም፡፡ “የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” የሚለው “ከቶ” ምን እንደሆነ አስተውሉ (ገላ 5፡16) “ምንም” ነውና፡፡

መንግሥቱን እንድንወርስ ከፈለግን ምንም የኃጢአት ፍላጎት መፈጸም የለብንም ”የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም…ስካር፥ ዘፋኝነት ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” (ገላ 5፡16-21) ብሏል፡፡ ብዙዎች ቀጥሎ በማቀርበው ምክር እንደሚከፋቸው እገምታለሁ፤ ክርስቶስ የሞተለትን ዓላማ መና የሚያስቀር ነገር ሠርተን ከመንግሥተ ሰማያት ከምንቀር፣ አንድ የማይጠቅም የሥጋ ሥራን ለማስቀረት ምክሩ ያስፈልገናል፣ ይጠቅመናልና ስሙኝ፡፡

ብዙዎች ለሚወዱት ሲነኩባቸው አይወዱም፤ ይህም ዘፈን ነው፡፡ ለዚህ ባሪያዎች የሆኑ አያሌ ናቸው፡፡ “ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ” (ሮሜ 6:16) እንዳለ መምረጥ ግድ ሊሆን ነው፡፡

ክርስቶስ ሞቶልኛል የሚል ምእመን ዘፈንን ግን እወዳለሁ ካለ የሞተለት አምላክ ለምን እንደሞተለት አልገባውም ማለት ነው፤ ጌታ የሞተው ለርስተ መንግሥተ ሰማያት ነው፣ ዘፈንና ዘፋኝነት ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ያስቀርብናል፡፡ ብዙዎች በሠርጋቸው፣ በልደታቸው፣ በደስታ ቀናት ይዘፍናሉ፣ ያዘፍናሉ፡፡ በዚህም ከክርስቶስ ይጣላሉ፡፡

ከርኩሰት ርኩሰት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን በበዓል ቀናት ምክንያት በማድረግ የሚዘፍኑት ነው፡፡ እንኳን እግዚአብሔርን ምክንያት አድርጎ ቀርቶ በማንኛውም ጊዜ እግዚአብሔር ዘፈንን እንደማይፈቅድ ያልተገነዘቡ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም የከለከለውን ነገር በእግዚአብሔር ቤት በመገኘትና መንፈሳዊ በዓልን ምክንያት አድርጎ መዝፈን ታላቅ ድፍረት ነው፡፡ ክርስቲያን በደስታው ቀን አምላኩን በመዝሙር ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡ በተቃራኒ ግን ለገና አዳር፣ ለጥምቀት አዳር፣ ለትንሣኤ አዳር፣ ታቦተ ሕጉ በሚወጣበት የጥምቀት በዓል፣ ለአዲስ ዓመት አዳር የዘፈን ዝግጅት ሲዘጋጁ ይስተዋላል፡፡

እንዲታወቅ የሚፈለገው ግን ዘፈን የእግዚአብሔር መመስገኛ ሳይሆን የሰይጣን መሆኑ ነው፡፡ ዘፈን በጨለማ ሥራ የተመደበበት ምክንያት የሰይጣን ድርሰትና ኃጢአት ሲሆን፤ ዘፈንን የማይሰማና የማይዘፍን የጨለማን ሥራ ከራሱ አስወግዷል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ ሲዘምሩ በሰይጣን የሚቃኙ ደግሞ ይዘፍናሉና፡፡

አንዳንዶች በዘፈን እግዚአብሔርን የሚያስደስቱ ስለሚመስላቸው፤ለሚቀጥለው ዓመት በዓል በሰላም ከደረስኩ በመዝፈን አከብራለሁ ሳይሉም አይቀሩ፤ ይህ ወንጌል “በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን” (ሮሜ 13፡13) እንዳለው በበዓሉ ቀን ሰክሮ መታየትና ዘፈን እየዘፈኑ ማደር ርኩሰት ከመሆኑ አልፎ ፈጣሪንና ሃይማኖቱን ማስነቀፍ ይሆናል፤ “በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ” (ሮሜ 2፡24)፡፡

ልብ በሉ! በታቦቱ ዙሪያ ሲዘፍኑ መገኘት፣ ሃይማኖቱ ዘፈን ይፈቅዳል ብሎ እንደመመስከር ስለሚሆን ሊቆም ይገባል፡፡ “ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር” አለን እንጂ ይዝፈን አላለንምና (ያዕ 5፡13)፣ የታደሉት በበዓላት ቀን ቅዳሴ ባለበት፣ እንዲሁም ከሚዘምሩ መዘምራን ጋር ተገኝተው ሲዘምሩ፤ ያልታደሉ ከጨለማ ልጆች ጋር ዘፈንን ሲዘፍኑ ያድራሉ ይውላሉ፡፡ ዘፈን የእግዚአብሔር መመስገኛ ሳይሆን የሰይጣን ግብር ነው፡፡ ውጤቱም ገሃነመ እሳት ያስገባል (ገላ 5፡15)፡፡

በዓላት በሚከበርበት ቦታ እንዴት ሊዘፍኑ ቻሉ ቢባል፣ ሰዎች ቀስ በቀስ ባህላዊ ነው፣ ባህላችንን አትንኩ፣… እያሉ ወደ ተቀደሰው ቦታ እንዳስጠጉት ይገመታል እንጂ፣ ጥንት እንዲህ አልነበረም፤ ሃይማኖቱም ይህንን አልፈቀደም፤ ከበጎ ነገር ጋር ማመሳሰልና ማስጠጋጋት የጠላት ዲያብሎስ ሥራ ነው፡፡ በስንዴው መካከል እንክርዳድን እንደሚዘራ በወንጌል ተመዝግቦአል (ማቴ 13፡25-40)፡፡

ስለዚህ “የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል” እንዳለው (ማቴ 24፡15) ቅዱስ በዓል በሚከበርበት ቦታ ርኩሰትን የሚያደርጉና የሚዘፍኑ ብርሃንን ከጨለማ ጋር ሊያቀላቅሉ የሚሹ ናቸው፡፡ አትዝፈኑ ተብሎ እየተደጋገመ እየተነገረ በአመጽ የሚሰሙ አልሆኑም፣ “የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፡፡ ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው” (2ኛ ጴጥ 2፡13-14)፡፡

ከእነዚህ ጋር ለመዝፈን አብሮአቸው የሚውልም ሆነ የሚያጅብ የተረገመ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ እርግማን ለመውጣት ንስሐ በመግባት ታቦቱን ከሚያከብሩ ካህናት፣ ከሚዘምሩ መዘምራን ጋር፣ እንዲሁም የልደትና የትንሣኤ በዓላት ሌሊት ቅዳሴና ውዳሴ ቤተ ክርስቲያን ብቻ በመገኘት መዘመር፣ ቅዳሴውን ወይም የመዝሙሩን ግጥሙን ባናውቀውም እንኳ በጭብጨባና በእልልታ ማጀብ ይገባናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” ይላልና (መዝ 1፡1) ከእነዚህ ከዘፋኞች፣ ከሌሊት ፓርቲ አዘጋጆች፣…በመለየት እርቃናቸውን ስናስቀራቸው፤ ሰው ለምን ወደ እነርሱ መምጣት እንደተወ ሲገባቸው ወደ እውነትም ይመለሳሉ፤ የምናጅባቸው እና ገንዘብ እየከፈልን ፓርቲያቸውን የምናደምቅላቸው ከሆነ በርቱ ግፉበት ብሎ እንደማበረታታት ይቆጠራልና “ወዳጅ ሆይ፥ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል” ያለውን ሕግ እንከተል (3ኛ ዮሐ 1፡11)፡፡

ወገኖቼ በዓል በመጣ ቁጥር የሚታሰበው ዘፈን፣ የሌሊት ስካር፣ የበዓላት ፈንጠዝያ ነው፡፡ በበዓላቶቻችን “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ” (ዘካ 8፡19) የተባልነው በጾም ፍቺዎቻችን ቀጥሎ በምናደርገው በዓላት “ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” (ኤፌ 5፡19)፣ በቅዳሴውም በመገኘት “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” (ቆላስ 3፡16) ተባልን እንጂ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኙ የዘፈን፣ የስካር፣ የዝሙት ርኩሰቶች በመፈጸም ከቅድስና ወደ ርኩሰት፣ ከመንግሥተ ሰማያት ወደ ገሃነም፣ ከእግዚአብሔር ወደ ዲያብሎስ ዘወር አንበል፡፡

ስለዚህ ወንጌል “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት … የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” (1ኛ ጴጥ 4፡3) ይላልና ሁላችንም “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ” (ኤፌ 5፡11) “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” (ሮሜ 12፡9) የሚሉትን አስተውለን ከጨለማ ጋር ላለመተባበር እንወስን፡፡

ባጠቃላይ “ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” (ኤፌ 5፡9-10) እንጂ ጌታን የሚያሳዝን፣ መንግሥተ ሰማያትን በሚያስቀርብን በዘፈንና በስካር ሕይወት አንመላለስ፡፡ ዘፈን ርኩሰት ነውና፣ ስካርና መዳራት ከጌታ ጋር ያጣሉናል፣ “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ” (1ኛ ሳሙ 2፡10) ከመንግሥተ ሰማያትም ውጪ ይሆናሉና ከእነዚህ ርኩት ሥራዎች በበዓላችን ቀን ላለማድረግ እንወስን፡፡

ዘፈን ላለመዝፈን፣ ላለመስከርና ርኩሰትን ላለመፈጸም ለሁላችንም ልብ ይስጠን፡፡ የንስሐ ዕድሜ ለሁላችንም አድሎ፣የልደትና የጥምቀት በዓልን በቅድስና እንድናከብር ሁላችንንም ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በበዓላት ቀን በመዝፈን ከጌታ ጋር አትጣሉ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

በበዓላት ቀን በመዝፈን ከጌታ ጋር አትጣሉ

ጽድቅ የሰፈነባትን፣ ድኅነትና የዘላለም ሕይወት የሚገኝባትን መንግሥተ ሰማያትን ሁላችን እንሻለን፡፡ ይህቺውም በጌታችን በአምላካችን፣ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተከፈተች የድኅነት መንገድ ናት፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ፈጣሪያችንን በማመንና በስሙ በመጠመቅ አንድ ጊዜ ይህቺን የዘላለም መንገድ እየተጓዝንባት እንገኛለን፡፡

ይህ የመንግሥተ ሰማያት በር የተከፈተው እንዲሁ በቀላሉ ሳይሆን በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ” ያለው (1ኛ ጴጥ 118-19)፡፡ አሁን በዚህ ውድ ልጁ ደም የተዋጀን ሁላችን የእርሱን ውለታ የምንመልሰው ባይሆንም፣ ፍቅራችንን የምንገልጽለት መንገድ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” (1ኛ ጴጥ 2:24) ተብሎአልና በጽድቅ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡

ፈጣሪያችን ከዲያብሎስ መዳፍ አላቆናል “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” (ቆላስ 1፡13-14) ከዚህ ከገባንበት መንገድ ሊያወጣን የሚችል ወጥመዶች ግን ተዘርግተውብናል፡፡ “በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋል” (1ኛ ጴጥ 3፡9) ተብለን ወደ መንግሥቱ የሚያስገባው ጥሪው ቢደርሰንም፣ ወደዚህ ሕይወት እንዳንገባ የሚያደርግ ሌላ እንቅፋት አለብን፡፡

ጥሪውን ሰምተን ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት የምንችለው፤ በጠሪው በእግዚአብሔር ፈቃድ ስንመላለስ እንደ ምክሩ ስንሄድ ብቻ ነው (1ኛ ተሰ 2፡11-12)፡፡ እግዚአብሔር ውድ ልጁን ለዓለም አንድ ጊዜ በመስቀል ሞቶ መንግሥቱ ከፍቶልናል፣ እኛም ይህን ፍቅር ቀምሰን አይተናል፤ ስለዚህ “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” (1ኛ ዮሐ 4፡19)፡፡ ነገር ግን ይህ ፍቅር የሚለካው እንደ ቃሉ ከሆነ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ 14፡15) ባለው ይረጋገጣል፡፡

እግዚአብሔር ደስ ለማሰኘት ምንም አይነት እርም ነገር ተሸክመን አንድንከተለው አያስፈልግም “በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኘውን ታደርግ ዘንድ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ስትሰማ፥ … እርም ከሆነው አንዳች ነገር በእጅህ አይንጠልጠልብህ” (ዘዳ 13፡17-18) ብሎናልና፡፡ አንጠልጥለን የምንከተለው ጸያፍ ነገር መኖር አይገባውም፡፡

ክርስቲያን የራሱን ደስታ ብቻ ሳይሆን፣ ፈጣሪን ምን ያስደስተዋል ብሎ በማስተዋል ይመለከታል፡፡ ለዚህ ነው ክቡር ዳዊት “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ” (መዝ 26፡4) ያለው፣ ፈጣሪን የሚያስደስተውን የሚያደርግ ደግሞ ከፈጣሪ ዘንድ ሁሉንም በረከት በመጨረሻም ያገኛል፡፡ “ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን” (1ኛ ዮሐ 3፡22) እንዳለ፡፡

መንግሥተ ሰማያትን የሚያስቀሩብን የሥጋ ፍላጎቶቻችን ናቸው፤ እነዚህም የሥጋ ፍላጎቶች በጎ ሥራዎች ሳይሆን ክፉ ምኞቶቻችን ሲሆኑ፣ ክርስቲያን ደግሞ “ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ” (1ኛ ተሰ 5፡22) የሚለውን መመሪያ መከተል አለበት፡፡ ክፉ የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስምና፡፡ “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል” (2ኛ ጢሞ 2፡22) የተባለው ከዚህ የተነሣ በመሆኑ ማናቸውንም የሥጋ ሥራ ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡

መንግሥተ ሰማያት ከሚያስቀር ጥቂት ከሚባል አናሣ የሥጋ ሥራም ቢሆን መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ጥቃቅን የምንላቸው የኃጢአት አይነቶችም ቢሆን በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናቸውና፡፡ እግዚአብሔር ጥቂት የኃጢአት እርሾ እንኳ እንዲኖርብን አይፈልግም፡፡ “የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” የሚለው “ከቶ” ምን እንደሆነ አስተውሉ (ገላ 5፡16) “ምንም” ነውና፡፡

መንግሥቱን እንድንወርስ ከፈለግን ምንም የኃጢአት ፍላጎት መፈጸም የለብንም ”የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም…ስካር፥ ዘፋኝነት ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” (ገላ 5፡16-21) ብሏል፡፡ ብዙዎች ቀጥሎ በማቀርበው ምክር እንደሚከፋቸው እገምታለሁ፤ ክርስቶስ የሞተለትን ዓላማ መና የሚያስቀር ነገር ሠርተን ከመንግሥተ ሰማያት ከምንቀር፣ አንድ የማይጠቅም የሥጋ ሥራን ለማስቀረት ምክሩ ያስፈልገናል፣ ይጠቅመናልና ስሙኝ፡፡

ብዙዎች ለሚወዱት ሲነኩባቸው አይወዱም፤ ይህም ዘፈን ነው፡፡ ለዚህ ባሪያዎች የሆኑ አያሌ ናቸው፡፡ “ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ” (ሮሜ 6:16) እንዳለ መምረጥ ግድ ሊሆን ነው፡፡

ክርስቶስ ሞቶልኛል የሚል ምእመን ዘፈንን ግን እወዳለሁ ካለ የሞተለት አምላክ ለምን እንደሞተለት አልገባውም ማለት ነው፤ ጌታ የሞተው ለርስተ መንግሥተ ሰማያት ነው፣ ዘፈንና ዘፋኝነት ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ያስቀርብናል፡፡ ብዙዎች በሠርጋቸው፣ በልደታቸው፣ በደስታ ቀናት ይዘፍናሉ፣ ያዘፍናሉ፡፡ በዚህም ከክርስቶስ ይጣላሉ፡፡

ከርኩሰት ርኩሰት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን በበዓል ቀናት ምክንያት በማድረግ የሚዘፍኑት ነው፡፡ እንኳን እግዚአብሔርን ምክንያት አድርጎ ቀርቶ በማንኛውም ጊዜ እግዚአብሔር ዘፈንን እንደማይፈቅድ ያልተገነዘቡ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም የከለከለውን ነገር በእግዚአብሔር ቤት በመገኘትና መንፈሳዊ በዓልን ምክንያት አድርጎ መዝፈን ታላቅ ድፍረት ነው፡፡ ክርስቲያን በደስታው ቀን አምላኩን በመዝሙር ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡ በተቃራኒ ግን ለገና አዳር፣ ለጥምቀት አዳር፣ ለትንሣኤ አዳር፣ ታቦተ ሕጉ በሚወጣበት የጥምቀት በዓል፣ ለአዲስ ዓመት አዳር የዘፈን ዝግጅት ሲዘጋጁ ይስተዋላል፡፡

እንዲታወቅ የሚፈለገው ግን ዘፈን የእግዚአብሔር መመስገኛ ሳይሆን የሰይጣን መሆኑ ነው፡፡ ዘፈን በጨለማ ሥራ የተመደበበት ምክንያት የሰይጣን ድርሰትና ኃጢአት ሲሆን፤ ዘፈንን የማይሰማና የማይዘፍን የጨለማን ሥራ ከራሱ አስወግዷል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ ሲዘምሩ በሰይጣን የሚቃኙ ደግሞ ይዘፍናሉና፡፡

አንዳንዶች በዘፈን እግዚአብሔርን የሚያስደስቱ ስለሚመስላቸው፤ለሚቀጥለው ዓመት በዓል በሰላም ከደረስኩ በመዝፈን አከብራለሁ ሳይሉም አይቀሩ፤ ይህ ወንጌል “በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን” (ሮሜ 13፡13) እንዳለው በበዓሉ ቀን ሰክሮ መታየትና ዘፈን እየዘፈኑ ማደር ርኩሰት ከመሆኑ አልፎ ፈጣሪንና ሃይማኖቱን ማስነቀፍ ይሆናል፤ “በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ” (ሮሜ 2፡24)፡፡

ልብ በሉ! በታቦቱ ዙሪያ ሲዘፍኑ መገኘት፣ ሃይማኖቱ ዘፈን ይፈቅዳል ብሎ እንደመመስከር ስለሚሆን ሊቆም ይገባል፡፡ “ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር” አለን እንጂ ይዝፈን አላለንምና (ያዕ 5፡13)፣ የታደሉት በበዓላት ቀን ቅዳሴ ባለበት፣ እንዲሁም ከሚዘምሩ መዘምራን ጋር ተገኝተው ሲዘምሩ፤ ያልታደሉ ከጨለማ ልጆች ጋር ዘፈንን ሲዘፍኑ ያድራሉ ይውላሉ፡፡ ዘፈን የእግዚአብሔር መመስገኛ ሳይሆን የሰይጣን ግብር ነው፡፡ ውጤቱም ገሃነመ እሳት ያስገባል (ገላ 5፡15)፡፡

በዓላት በሚከበርበት ቦታ እንዴት ሊዘፍኑ ቻሉ ቢባል፣ ሰዎች ቀስ በቀስ ባህላዊ ነው፣ ባህላችንን አትንኩ፣… እያሉ ወደ ተቀደሰው ቦታ እንዳስጠጉት ይገመታል እንጂ፣ ጥንት እንዲህ አልነበረም፤ ሃይማኖቱም ይህንን አልፈቀደም፤ ከበጎ ነገር ጋር ማመሳሰልና ማስጠጋጋት የጠላት ዲያብሎስ ሥራ ነው፡፡ በስንዴው መካከል እንክርዳድን እንደሚዘራ በወንጌል ተመዝግቦአል (ማቴ 13፡25-40)፡፡

ስለዚህ “የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል” እንዳለው (ማቴ 24፡15) ቅዱስ በዓል በሚከበርበት ቦታ ርኩሰትን የሚያደርጉና የሚዘፍኑ ብርሃንን ከጨለማ ጋር ሊያቀላቅሉ የሚሹ ናቸው፡፡ አትዝፈኑ ተብሎ እየተደጋገመ እየተነገረ በአመጽ የሚሰሙ አልሆኑም፣ “የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፡፡ ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው” (2ኛ ጴጥ 2፡13-14)፡፡

ከእነዚህ ጋር ለመዝፈን አብሮአቸው የሚውልም ሆነ የሚያጅብ የተረገመ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ እርግማን ለመውጣት ንስሐ በመግባት ታቦቱን ከሚያከብሩ ካህናት፣ ከሚዘምሩ መዘምራን ጋር፣ እንዲሁም የልደትና የትንሣኤ በዓላት ሌሊት ቅዳሴና ውዳሴ ቤተ ክርስቲያን ብቻ በመገኘት መዘመር፣ ቅዳሴውን ወይም የመዝሙሩን ግጥሙን ባናውቀውም እንኳ በጭብጨባና በእልልታ ማጀብ ይገባናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” ይላልና (መዝ 1፡1) ከእነዚህ ከዘፋኞች፣ ከሌሊት ፓርቲ አዘጋጆች፣…በመለየት እርቃናቸውን ስናስቀራቸው፤ ሰው ለምን ወደ እነርሱ መምጣት እንደተወ ሲገባቸው ወደ እውነትም ይመለሳሉ፤ የምናጅባቸው እና ገንዘብ እየከፈልን ፓርቲያቸውን የምናደምቅላቸው ከሆነ በርቱ ግፉበት ብሎ እንደማበረታታት ይቆጠራልና “ወዳጅ ሆይ፥ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል” ያለውን ሕግ እንከተል (3ኛ ዮሐ 1፡11)፡፡

ወገኖቼ በዓል በመጣ ቁጥር የሚታሰበው ዘፈን፣ የሌሊት ስካር፣ የበዓላት ፈንጠዝያ ነው፡፡ በበዓላቶቻችን “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ” (ዘካ 8፡19) የተባልነው በጾም ፍቺዎቻችን ቀጥሎ በምናደርገው በዓላት “ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” (ኤፌ 5፡19)፣ በቅዳሴውም በመገኘት “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” (ቆላስ 3፡16) ተባልን እንጂ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኙ የዘፈን፣ የስካር፣ የዝሙት ርኩሰቶች በመፈጸም ከቅድስና ወደ ርኩሰት፣ ከመንግሥተ ሰማያት ወደ ገሃነም፣ ከእግዚአብሔር ወደ ዲያብሎስ ዘወር አንበል፡፡

ስለዚህ ወንጌል “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት … የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” (1ኛ ጴጥ 4፡3) ይላልና ሁላችንም “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ” (ኤፌ 5፡11) “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” (ሮሜ 12፡9) የሚሉትን አስተውለን ከጨለማ ጋር ላለመተባበር እንወስን፡፡

ባጠቃላይ “ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” (ኤፌ 5፡9-10) እንጂ ጌታን የሚያሳዝን፣ መንግሥተ ሰማያትን በሚያስቀርብን በዘፈንና በስካር ሕይወት አንመላለስ፡፡ ዘፈን ርኩሰት ነውና፣ ስካርና መዳራት ከጌታ ጋር ያጣሉናል፣ “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ” (1ኛ ሳሙ 2፡10) ከመንግሥተ ሰማያትም ውጪ ይሆናሉና ከእነዚህ ርኩት ሥራዎች በበዓላችን ቀን ላለማድረግ እንወስን፡፡

ዘፈን ላለመዝፈን፣ ላለመስከርና ርኩሰትን ላለመፈጸም ለሁላችንም ልብ ይስጠን፡፡ የንስሐ ዕድሜ ለሁላችንም አድሎ፣የልደትና የጥምቀት በዓልን በቅድስና እንድናከብር ሁላችንንም ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር